ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመርጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በጉጉት እንደሚጠብቁ ገለጹ

AMN- ግንቦት 22/2018 ዓ.ም

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርድ የወሰዱ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ ሰርቶ የሚያሰራቸውንና የወጣቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሪ ለመምረጥ ግንቦት 24 ቀንን በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት ከተመዘገቡ ዜጎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ በሂደቱ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ተነሳሽነትና ዝግጅት ለኤ ኤም ኤን አብራርተዋል።

ወጣቶቹ የምርጫ ካርድ የወሰዱት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንቦት 24 ቀን የሚካሄደውን ምርጫ በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት እመቤት አለሙ በሰጠችው አስተያየት፣ የምርጫ ካርድ ስትወስድ ይህ የመጀመሪያዋ መሆኑን ገልጻለች።

ሂደቱና አጠቃላይ ድባቡ በጣም ደስ የሚልና የሚያጓጓ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ መጠን የምርጫውን ዕለት በጉጉት እየጠበቅን ነው ስትል የምርጫው ሂደት ውስጣዊ ገፅታ ምን እንደሚመስል በገሃድ ለማየት መጓጓቷን ገልጻለች።

ሌላኛዋ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፍሬዘር አለባቸው በበኩሏ፣ ከዚህ ቀደም ዕድሜዋ ባለመድረሱ ምክንያት በምርጫ መሳተፍ እንዳልቻለች አስታውሳለች።

በፊት ስለ ምርጫ ከታላላቆቼ ብቻ ነበር የምሰማው፤ አሁን ግን ራሴ በቦታው ተገኝቼ ካርድ ወስጃለሁ፤ ይህ ትልቅ ልዩነት አለው” ብላለች።

አክላም ሰርቶ የሚያሰራኝንና እንደ ወጣትነቴ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድደርስ የሚያግዘኝን ፓርቲ ለመምረጥ ግንቦት 24ን በጉጉት እጠብቃለሁ ስትል ዝግጁነቷን አረጋግጣለች።

በተመሳሳይ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሙና አለማር፣ በምርጫው ለመሳተፍ ካርዷን ይዛ መዘጋጀቷን ገልጻለች።

በወጣቶች እና በደሃው ማህበረሰብ ላይ ትኩረት የሚያደርገውን አይቼ ለመምረጥ ዝግጁ ነኝ፤ በዕለቱም በማለዳ ተገኝቼ ድምፅ ለመስጠት እየጠበቅኩ ነውም ብላለች።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ታደሰ መንግስቱ በበኩሉ፣ በአንድ ሀገር ላይ የተረጋጋ ህይወት መኖር የሚቻለው ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሲኖር መሆኑን ተናግሯል።

ወጣቱ ከምንም በላይ በምርጫው ላይ መሳተፉ የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር የጠቀሰው ታደሰ፣ ወደፊት የተሻለች ሀገር ለማግኘት በዚህ ምርጫ ላይ መሳተፍ ግድ ነው።

ስለዚህ ወጣቱ ያለምንም መሸማቀቅና ወደኋላ ሳይል፣ ለራሱና ለሀገሩ የሚበጀውን መሪ ለመምረጥ ዝግጁ መሆን አለበት ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ወጣቱ አክሎም ግንቦት 24 ለሀገሪቱ እድገትን የሚመኝ መሪ የሚመረጥባት ዕለት በመሆኗ፣ ወጣቶች ካርዳቸውን አዘጋጅተው ሊጠብቋት እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review