በካርዳችን የሀገርን መጻኢ ዕድል ለመወሰን በጉጉት እየጠበቅን ነው – የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

You are currently viewing በካርዳችን የሀገርን መጻኢ ዕድል ለመወሰን በጉጉት እየጠበቅን ነው – የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

AMN – ግንቦት 23/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱን ቀጣይ የጉዞ አቅጣጫ የሚወስኑበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነገ ይካሄዳል።

ይህን ታሪካዊ ዕለት በከፍተኛ ተስፋና ጉጉት እየተጠባበቁ የሚገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት፤ የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት በተለየ መልኩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታየበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ወጣት መቅረዝ ሰለሞን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እጅግ ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሳ፤ የምርጫው ዕለት እስኪመጣ ድረስ በከፍተኛ ጉጉትና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እየጠበቅን ነው ብላለች።

ማኅበረሰቡ የተሻለውን አማራጭ መምረጥ እንዲችል ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የገለጹት አቶ ዳመነ ሙሉጌታ ፤ በራሴ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ለአመንኩበት ፓርቲት ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

በዕለቱ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በምርጫ ጣቢያው ተገኝቼ ቀጣይ አምስት ዓመት እንዲያስተዳደር የምፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ፀሐይ ኃይሉ ናቸው፡፡

የተሰጠንን የምርጫ ዕድል በአግባቡና በሥርዓቱ እንድንጠቀምበት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረውልናል ያሉት ወ/ሮ ፀሐይ ፣ ምርጫው ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግር መሪ የምንሰይምበት በመሆኑ ሁሉም ሰው ወጥቶ ድምፁን መስጠት እንዳለበትም ጥሪ አድርገዋል።

ሌላዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወ/ሮ ኤልሣ የዘንድሮው ምርጫ የቅስቀሳ ሂደት ዲጂታላይዝድ (ዘመናዊ) የሆነና ሥልጣኔ የተሞላበት ስለነበር ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የአመዘጋገቡ ሥርዓት፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ አወቃቀርና አደረጃጀት ከዚህ ቀደም ካየናቸው ምርጫዎች አንጻር እጅግ የላቀና የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review