የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሻውን ለመወሰን መካሪና ገሳጭ እንደማያስፈልገው አሳይቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሻውን ለመወሰን መካሪና ገሳጭ እንደማያስፈልገው አሳይቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ግንቦት 24/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ህዝብ በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ ሀገረ መንግስቱንና የዲሞክራሲ ስርዓቱን ለመገንባት የሚሻውን ለመወሰን የውጭ መካሪም ሆነ ገሳጭ እንደማያስፈልገው በተግባር ያሳየበት መሆኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚወዳደሩበት አካባቢ በሻሻ ተገኝተው ድምፅ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት፥ በአሁኑ ወቅት ከመራጩ ህዝብ ይልቅ የተመራጮች ዝግጁነት ይበልጥ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

ህዝቡ በቁርጠኝነትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የራሱን ምርጫ ካደረገ በኋላ፥ የተመረጡት አካላት በዚያው ልክ ታምነው፣ በንጹህ ልብና እጅ፣ ሳይታክቱና ሳይደክሙ የታላቁን ህዝብ ውለታ ለመክፈልና ታሪክ ለመቀይር ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? የሚለው ዋናው ጥያቄ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ጉዳዩ የእልህ፣ የቁጣ፣ የክርክር ወይም ‘አሸንፋለሁ’ የማለት ሳይሆን፥ እራሱን አሳልፎ የሰጠንን ህዝብ እንዴት በታማኝነት አገልግለን ህይወቱን እንለውጣለን የሚለው ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እጩ ተወዳዳሪዎች ሁሉ ከየትኛውም ወገን ይሁኑ ይህንን ከባድ ሀላፊነት ተገንዝበው ሊሰናዱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የጥንት አቋም በእጅጉ የተለየች መሆኗን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መጪዎቹ አምስት ዓመታት የሀገሪቱ በርካታ የታሪክ እጥፋት የሚታይባቸው በመሆናቸው ካለፈው በበለጠ መልፋት፣ መድከም፣ ማሰብና መደመርን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review