AMN ግንቦት 24/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምርጫ ክልላቸው ተገኝተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ከንቲባዋ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ ማለዳ በይፋ በተጀመረው የድምፅ መስጠት ሂደት መራጮች ሉዓላዊ መብታቸውን በተግባር እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ይጠቅመኛል፣ ይመራኛል የሚለውን መሪ ያለምንም ተፅዕኖ እና ጫና በደስታና በነፃነት በመምረጥ የዲሞክራሲ ተሳትፎውን እያጠናከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ እውነተኛ፣ ገለልተኛ እና ህዝብን ሉዓላዊ ያደረገ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሽግግር ላይ መድረሷን ያሳየበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ከንቲባዋ በንግግራቸው አንስተዋል።
የስልጣን ምንጭ ከሕዝብ ድምፅ ውጪ ሌላ ሊሆን እንደማይችል የኢትዮጵያ ሕዝብ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ ይህም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማት እና ታላላቅ ሀገራዊ ራእዮችን ለማሳካት ወሳኝ መደላድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የድምፅ መስጫ ሰዓት ከመጠናቀቁ በፊት መራጮች መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የምርጫ ካርዳቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

የምርጫ ካርድ ማባከን መብትን ማባከን እንደሆነ ያመለከቱት ከንቲባዋ ፣ ዜጎች ነገ እንደፈለጉት በሙሉ መብት ሆኖ ልማትን፣ መብትንና ሰላምን ለማስከበር እንዲሁም ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዛሬ ውሳኔያቸውን በድምፅ መግለጽ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸ