AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን በየዓመቱ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጁን 5 ይከበራል። ዕለቱ አካባቢን ከብክለት ነጻ ለማድረግ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ነው፡፡
ዘንድሮም ቀኑ ሲከበር የካርበን ልቀትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን በአየር ንብረት ዙሪያ ስለሚኖሩ ግንኙነት ሥርዓቶች ላይ እንደገና ማሰብ ማተኮር እንደሚገባ ተመድ ገልጿል፡፡
ይህ ሁኔታ የተፈጥሮን እና የከተማ ልማትን ሚዛናቸውን አስጠብቆ ለማስኬድ በአዲስ የከተማ እሳቤ ውስጥ እያለፈች ላለችው አዲስ አበባ ልዩ ትርጉም ይሰጣል፡፡
በአዲስ አበባ እየተተገበሩ ያሉ ሰፋፊ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ስነ-ምህዳር በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ለዓመታት የፍሳሽ እና የደረቅ ቆሻሻ መጣያ እንዲሁም ለጎርፍ አደጋ አጋላጭ የነበሩት የአዲስ አበባ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች በቅርብ ዓመታት እየተከናዎኑ ባሉ ሥራዎች ይህ ታሪካቸው እየተቀየረ ነው፡፡

የብክለት ምንጭ የነበሩትን የወንዝ ዳርቻዎች ወደ ውብ መዝናኛዎች፣ የብስክሌት መስመሮችና የህዝብ መናፈሻዎች በመቀየር ከተማዋ ንጹህ አየር እንድትተነፍስ እየተደረገ ነው።
የወንዞች ዳርቻን በማጽዳት የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ ዕፅዋት እየተተከሉባቸው ሲሆን፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶቹ የከተማዋን የውሃ አካላት ከብክለት እያላቀቁ ናቸው።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ሰፊ የኮሪደር ልማት ከመሠረተ-ልማት ግንባታ ባሻገር ትልቅ የአካባቢ ጥበቃ አካልም ነው፡፡

በኮሪደር ልማቱ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተዘጋጁ አረንጓዴ ሥፍራዎች የመዲናይቱን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።
ሰፋፊ እግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች መገንባታቸው ነዋሪዎች ከሞተር ተሽከርካሪዎች ይልቅ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የመጓጓዣ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ያበረታታል። ይህ ደግሞ የአየር ብክለትን መቀነስ የሚያስችል ነው።
የኮሪደር ልማቱ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶችንና ዘመናዊ የመፀዳጃ ሥፍራዎችን በየቦታው በማካተቱ ህዝቡ የአካባቢውን ንጽህና የመጠበቅ ልምዱ እየዳበረ እንዲመጣ አድርጓል።

በቅርቡ እንደተመረቀው የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት አይነት ወንዞችን ተከትለው የሚሰሩ ስራዎች ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸው፣ አካባቢን እየጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያዎች ናቸው፡፡
የዘንድሮውን የአካባቢ ቀን ስናከብር አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት እና በወንዝ ዳርቻዎች ፕሮጀክቶች አማካኝነት ይበልጥ አረንጓዴ፣ ንፁህ እና ለኑሮ ምቹ እየሆነች መምጣቷን የምናስተውልበት ነው፡፡