የዛሬው ድምፅ፣ የነገ ውርስ መሆኑ የገባቸው እናቶች…

You are currently viewing የዛሬው ድምፅ፣ የነገ ውርስ መሆኑ የገባቸው እናቶች…

AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

እናቶች ዛሬ ያኖሩት እያንዳንዱ የጣት አሻራ እና የሰጡት እያንዳንዱ ድምፅ፣ ነገ ለልጆቻቸው የሚያቆዩት ታላቅና የማይጠፋ ውርስ ነው።

ዛሬ በጀርባ እና በሆድ የታዘሉ ሕፃናት ነገ አድገው ሃገራቸውን በነፃነትና በክብር እንዲረከቡ፣ እናቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፀሐይና በደመና ሳይበገሩ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተገኝተው ድምጻቸውን በነፃነት ሰጥተዋል፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በየምርጫ ጣቢያዎቹ የታየው ትዕይንት ተራ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም የእናትነት ፍቅር ከሀገር ፍቅር ጋር የተሳሰረበት ታሪካዊ ምዕራፍ እንጂ።

እናቶች ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለውና አቅፈው ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲያመሩ በእጃቸው የያዙት የዛሬውን የምርጫ ወረቀት ብቻ አይደለም፤ በውስጡ የልጆቻቸውን የነገ ብሩህ ተስፋ ጭምር ነው።

አንዲት እናት ለልጆቿ የምትመኘው ሰላምን፣ እድገትን እና የተረጋጋች ሀገርን ነው። ለልጆቻቸው የተሻለች፣ የበለጸገችና በዲሞክራሲ ሥርዓት የጠነከረች ሀገርን የማስረከብ ትልቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው የተረዱት እናቶች፣ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዋነኛው መንገድ በምርጫ መሳተፍ እና ድምፅን በነፃነት መስጠት መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።

ይህንኑ ታላቅ አደራ ለመወጣት የቤት ውስጥ ሥራዎቻቸውን ወደ ጎን በመተው ጨቅላ ሕፃናትን በጀርባቸው አዝለው ረጅም ሰልፎችን በጽናት ጠብቀዋል።

በፀሐይና በደመና ሳይበገሩ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተገኝተው ድምጻቸውን የሰጡት እናቶች፣ የነገዋ ኢትዮጵያ የሰላም እና የልማት ሀገር እንድትሆን መሰረት ጥለዋል።

እናቶች ዛሬ ያኖሩት እያንዳንዱ የጣት አሻራ እና የሰጡት እያንዳንዱ ድምፅ፣ ለነገ ለልጆቻቸው የሚያቆዩት ትልቅና የማይጠፋ ውርስ ነው። ዛሬ በጀርባቸው የታዘሉት ሕፃናት ነገ አድገው አገራቸውን በነፃነትና በክብር እንዲመሩ፣ ዛሬ የተሰጠው ድምፅ የሰላምና የዲሞክራሲ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል።

ይህ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የእናቶች ንቁ ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት፣ እናቶች በሀገር ግንባታ እና በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና በድጋሚ ያረጋገጠ ደማቅ አሻራ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review