AMN ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነ፣ የሕዝባችንን የጤና አገልግሎት በአዲስ ከፍታ ላይ የሚያስቀምጥ አዲስ የዲኤንኤ(DNA)፣ የፎሬንሲክና ስነምረዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡
ሀገራችን ብዙ የውጭ ምንዛሪ የምታጣበት እና የምርመራ ውጤት ለማግኘት በጣም ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን ችግር የሚያስቀር የDNA መረጃ ማከማቻና ማነጻጸሪያ ሲስተም (CODIS)፣ በወንጀል የተጠረጠሩ፣ ወላጅነትን ለማረጋገጥና ተመሳሳይ ምርመራዎችን በዘር መለያ (DNA Profiling) ለመለየት፣ የቤተሰብ ግንኙነትን እስከ ዘር ሀረግ መለየትና ማረጋገጥ እንዲሁም አጠራጣሪ ማንነትን ለማወቅ የሚያስችል የልህቀት ማዕከል ነው።

ይህ ማዕከል የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ምርመራን ውጤታማ በማድረግና በማዘመን፣ በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የወንጀል ምርመራ ለማካሄድ፣ የመብት ጥያቄዎችን ለመመለስና ለሕዝብ ጤና ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ብሔራዊ የልህቀት ማዕከል ነው ብለዋል፡፡
ሁሌም ቃልን በተግባር ፈፅመን በቁርጠኝነትና በተሻሻለ የስራ ባህል እየሰራን ባለፉት 5 ዓመታት ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት 4 ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥኑ ሆስፒታሎች በመገንባትና ነባሮቹንም ሆስፒታሎች በማደስና በማስፋፋት ሰፊ ስራዎችን ሰርተን አዘምነናቸዋል፡፡

በከተማ አስተዳደራችን በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያን የዕድገት ተምሳሌትነት እና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ምዕራፍ እያበሰርን ነው! ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የጤና ባለሙያዎቻችንን ትጋት፣ ብቃት እና እምነት ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን።
ከእቅድ ጀምሮ የልህቀት ማዕከሉ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን በሙሉ በራሴ፣ በከተማ አስተዳደሩ እና በተጠቃሚዎች ስም ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡