AMN ግንቦት 29/2018
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍና የሕዝብን ሰላም ለማደፍረስ ጽንፈኛ ኃይሎችና የውጭ ጠላቶች የከፈቱት ሁለንተናዊ ጥቃት መክሸፉን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ሀገራዊ ለውጡን የማይቀበሉ አካላት በመሬት ላይ የሽብር ጥቃቶችን ከመፈጸም ጀምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፕሮፓጋንዳና የሥነ-ልቦና ጦርነት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫውን የህልውና እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማረጋገጫ አድርጎ በመውሰድ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በአንጻሩ የስልጣን ሽግግርን በድምጽ መስጫ ኮሮጆ ሳይሆን በኃይል ለመጠቅለል የሚሹ የውስጥ ቅጥረኞችና የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የውጭ ኃይሎች ሂደቱን ለማስቆም ከምርጫው በፊት፣ ወቅትና በኋላ ከፍተኛ ሴራዎችን መሸረባቸውን ይፋ አድርጓል።
አፍራሽ ኃይሎቹ የመንግሥትን ሕጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣትና ኢትዮጵያን ወደ ሥርዓት አልበኝነት ለመክተት ሕዝቡ የምርጫ ካርድ እንዳይወስድ፣ በፖለቲካ ድጋፍ ሰልፎች ላይ እንዳይገኝ እና በምርጫው ቀን ድምጽ እንዳይሰጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ተጠቅሷል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ህሕብ ለጥሪዎቻቸው እውቅና ባለመስጠትና የጽንፈኝነትን አጀንዳ ውድቅ በማድረግ፥ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ተሳትፎ የምርጫ ካርድ በመውሰድ፣ በሰልፎች ላይ በነጻነት በመገኘትና በምርጫው ቀን በነቂስ ወጥቶ ድምጽ በመስጠት አፍራሽ ኃይሎቹን ማሸነፉን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ይህ የዲሞክራሲ ስኬት ያለመስዋዕትነት እንዳልመጣ የጠቀሰው የሰላም ሚኒስቴር፤ የጸጥታ ተቋማት ባደረጉት ወቅቱን የጠበቀና የተቀናጀ አጸፋዊ እርምጃ የሽብር ዕቅዶቹ ሊከሽፉ መቻላቸውን አስታውቋል።
ሆኖም የሕዝቡን አብሮነት ለመስበር የተሞከሩ የሽብር ጥቃቶች እንደነበሩ ጠቅሶ፤ ህዝቡ የከፈለው መስዋዕትነት ጽንፈኝነትን በመቃወም ሀገርን የሚያስቀጥል ሕጋዊ መንግስት ለመመስረት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየበት መሆኑም ተመልክቷል።