የኢትዮጵያ የተቀናጀ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ውጤታማ የኢኮኖሚ አስተዳደርን በማስፈን ፈጣን ዕድገት እንዲመዘገብ አስችሏል

You are currently viewing የኢትዮጵያ የተቀናጀ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ውጤታማ የኢኮኖሚ አስተዳደርን በማስፈን ፈጣን ዕድገት እንዲመዘገብ አስችሏል

AMN ሰኔ 4/2018

የኢትዮጵያ የተቀናጀ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ውጤታማ የኢኮኖሚ አስተዳደርን በማስፈን ፈጣን ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 25ኛ መደበኛ ስብሰባውን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ በሚያቀርቡት የበጀት መግለጫ ላይ እየተወያየ ይገኛል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በመግለጫቸው፤በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የፌዴራል መንግሥት የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ መግለጫ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዞና የተያዘው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕይታና አፈፃጸም በማመላከት ተደግፎ የቀረበውን የቀጣይ በጀት ዓመት የበጀት ድልድል የተመሰረተባቸውን ታሳቢዎች በዝርዝር አቅርበዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ስኬታማ ትግበራ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በብቃት በመቋቋም ጠንካራ አፈጻጸምና ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም ከ2012 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በየዓመቱ የ6 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፤ በ2017 ደግሞ የ9 ነጥብ 2 በመቶ አስደናቂ ዕድገት አስመዝግቧል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከመካከለኛው ምሥራቅ የመነጩ ጫናዎችንም ጭምር በመቋቋም የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚመዘገብ አስታውቀዋል።

ይህም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ከሚገኙ የዓለም ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚያሰልፋት ስኬታማ የዕድገት ጉዞ ላይ መሆኗን እንደሚያሳይ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ፈጣን የዕድገት ጉዞም የዋጋ ንረትን በመግታት ስኬታማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመተግበርና ምርታማነትን በማሳደግ የመጣ መሆኑን ልዩ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

የተቀናጀ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ትግበራ፣ የምርታማነት በማሻሻልና ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ የዋጋ ግሽበትን በተሳካ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

የተወሰዱ እርምጃዎችም ሸቀጦችና የአገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ በማውረድ አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱን አስታውቀዋል።

በግብርና ዘርፍም በሰብልና እንስሳት ምርት አቅርቦት ሰንሰለት ውጤታማነት በማሳደግና የከተማ ግብርናን በማበረታታት የዋጋ ንረትን በመቀነስ ለዜጎች እፎይታን በመፍጠር ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በባንኮች የሚሰጡ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ብድር የተገደበ ዕድገት እንዲኖረው በማድረግ የገንዘብ አቅርቦቱ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን መደረጉ የዋጋ ንረትን እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ የሚወሰድ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም መደረጉ የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ በማውረድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስተዋል።

በዚህም በነሐሴ 2014 ዓ.ም ወደ 34 ነጥብ 5 በመቶ አሻቅቦ የነበረውን አጠቃላይ የዋጋ ንረት በመጋቢት 2016 ዓ.ም ወደ 9 ነጥብ 4 በመቶ ነጠላ አሃዝ ዕድገት ማውረድ መቻሉን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱም የኢትዮጵያ ስታስቲስክስ በየወሩ በሚያወጣው የሸማቾች ዋጋ ኢንዴክስ መሰረት ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ላይ የታየው ቅናሽ አዎንታዊ ውጤቱን በግልፅ እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሬ ለውጡም የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ቀድሞውኑ የተቀናጀ ስራ በመስራት የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠር የተቻለበት መሆኑን መጥቀሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም ይበልጥ የተረጋጋና የበለጸገ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ የሚያጠናክር ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review