የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለታጠቁ ኃይሎችና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አዲስ ጥሪ አቀረበ

AMN – ሰኔ 04/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር አቀፍ እና በክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ የአጀንዳ ቀረጻ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራ ማጠናቀቁን ያስታወቀ ሲሆን፤ የምክክር ጉባኤው በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጿል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በሰጡት መግለጫ፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የተገኘበትና እጅግ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱም እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 234 ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በክልሎች በተካሄዱ መርሃ ግብሮች ላይ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሰራተኞች ማህበራት፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በንቃት መሳተፋቸውን ፕሮፌሰር መስፍን አስረድተዋል።

አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ ላይ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን እየተፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ወደ ውይይቱ ላልገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

እነዚህ አካላት የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት አሁንም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በየአካባቢው የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎችም የትጥቅ አማራጭን ትተው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡና አጀንዳዎቻቸውን በምክክር መድረኩ ላይ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ሁኔታውን ሲያስረዱ ወደ ሰላሙ መድረክ የመጡትን ታጣቂዎች አጀንዳ እየተቀበልን የሂደቱ ተሳታፊ እያደረግናቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአጀንዳ ቀረጻ ግብዓቶችን ያሰባሰበው ኮሚሽኑ፣ በቀጣዩ ስራው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን በይፋ መጥራት መሆኑንና ጉባኤው የሚጀምርበትም ቀን በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል።

ይህ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሁሉንም አሸናፊ አድርጎ የሚያወጣ ታሪካዊ ሂደት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ለጉባኤው መሳካት የሲቪል ማህበረሰቡና የተለያዩ ተቋማት እገዛ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review