የጉባው ብስራት… በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ

AMN -ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና ፖሊሲዎችን በስፋት በመተግበር ላይ ትገኛለች።

ይህም ሀገሪቱ በራሷ አቅምና ሃብት ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት እንድታስመዘግብ ከመደገፉም በላይ፣ ውጫዊ የኢኮኖሚ ጫናዎችን በጽናት የመመከትና የመቋቋም አቅሟን እንደሚያጎለብተው ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በቀጣይ የምትተገብራቸውን 7 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ማብሰራቸው ይታወሳል።

በሚቀጥሉት አምስት እና ስድስት ዓመታት የሚተገበሩት እነዚህ ሰባቱ የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች፤ የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ ማስመረቅ፣ የነዳጅ ማጣሪያ እውን ማድረግ፣ ሁለተኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር እና በመላው ሀገሪቱ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ግንባታን ማካተት ናቸው፡፡

እነዚህ የሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የኢኮኖሚ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠናክሩት መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካትም በአፍሪካ ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ባለፈው ጥር 2/2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንባታውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ የያዘችው በርካታ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ወደፊት የአፍሪካ ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት ማዕከል ለመሆን ያለመ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ 3 ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ እየተገነባ ይገኛል።

12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣበት የአውሮፕላን ማረፊያው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

አውሮፕላን ማረፊያው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፣ ይህም አሁን ካለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የማስተናገድ አቅም ጋር ሲነጻጸር በ4 ነጥብ 4 እጥፍ ብልጫ ይኖረዋል።

የዚህን ግዙፍ ፕሮጀክት የስራ ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስፍራው በመገኘት ተመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምልከታቸው ወቅት፤ ፈተናዎችን በቅርበት እየፈታን ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካ ማሰብ፣ ማቀድ፣ መስራት እና ማሳካት እንደምትችል ለዓለም የምናሳይበትና አፍሪካን የምናነቃቃበት ግዙፍ ስራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ታሪክ በግዝፈቱ፣ በሀብት ፍሰቱና በማሽነሪ ብዛቱ ቀዳሚ የሆነው የቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስፍራው ከ8 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዲሁም እስከ 4 ሺህ የሚጠጉ ማሽነሪዎችና መኪናዎች በስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቱን ግዙፍ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ የእያንዳንዱ መኪና እንቅስቃሴና የስራ ውሎ በድሮንና በዳሽቦርድ አማካኝነት በቨርቹዋል ቀጥታ ቁጥጥር እየተደረገበት ይገኛል።

ይህ አይነቱ የኦፐሬቲንግ ሲስተም በሀገሪቱ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉትን የመዘግየትና የተጨማሪ ወጪ ችግሮች ለመቅረፍ እንዲሁም ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ እንደ ትልቅ ማሳያ የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ “አትችሉም” የሚል ምልከታን በመደመር እሳቤ እያሸነፈች፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች እና በተያዘለት ጊዜ እያጠናቀቀች ቃልን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።

እንደ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ ኢትዮጵያን ከዓለም አቪዬሽን መሪዎች ተርታ በማስቀመጥ የኢኮኖሚ ነጻነትን የሚያረጋግጡ ለትውልድ የሚሻገሩ ናቸው፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review