AMN ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም
800 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል እየተካሄደ በሚገኘው መረሃ ግብር የተሳተፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር)፤ መርሃ ግብሩ የከተማዋን የጎርፍ ተጋላጭነት የቀነሰ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከለውጡ በፊት የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ3 በመቶ በታች እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ ባለፉት ተከታታይ አመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ23 በመቶ በላይ ማደግ መቻሉን ገልፀዋል።
የአንድ ከተማ ስማርት ከተማነት የሚገለፀው የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነቱ የቀነሰ መሆን፣ ከመሰረተ ልማት ዕድገት ባሻገር የሚታየው የአረንጓዴ ሽፋን እና ለአደጋ ስጋት ያልተጋለጠ መሆን መቻሉ ነው ብለዋዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታዲያ እነዚህን መስፈርቶች ለማሟላት የሚያግዝና አዲስ አበባ የጀመረችውን የስማርት ከተማነት ጉዞ የሚያሳልጥ ስለመሆኑ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

ከተማ የሚገነባው ለሰው ነው ያሉት ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር)፤ የአየር ንብረቷን ምቹነት ያላረጋገጠች ከተማ የስማርት ከተማነት ሂደት ሰንካላ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አዲስ አበባ ከተማ በመልካም አስተዳደር፣ በመሰረተ ልማት ዕድገትና በመሰል ዘርፎች ያሳየችውን ለውጥ በአረንጓዴ ሽፋን ላይም እየደገመች እንደምትገኝ ገልፀዋል።
ከተማዋ ቀደም ሲል በሸማችነት ብቻ የምትታወቅበትን ባህሪ በመቀየር አምራችም ጭምር እየሆነች ትገኛለች ብለዋል። ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ ሚና የጎላ እንደሆነ አብራርተዋል።
በላይሁን ፍስሃ