የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ፣ የንግድ ሥርዓቱን ለመግራትና ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር በትኩረት ይሠራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN-ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

በሚቀጥሉት 90 ቀናት በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ፣ የንግድ ሥርዓቱን የመግራትና ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን የመቆጣጠር ሥራ በትኩረት ይከናወናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በቀጣዮቹ 90 ቀናት መሪ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን ወደ ተግባርም አስገብቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣በድህረ ምርጫ በፍጥነት ፊታችንን ወደ ሥራ በመመለስ ፈጣን ውጤቶችን ማስመዝገብ፣ ተከታታይና አዳዲስ ነገሮችን መተግበር፣ ህብረተሰባችን ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በላቀ ትጋትና ያለ እረፍት መፈጸም የሚያስችል እቅድ ይዘን በልዩ ትኩረት የምንፈፅም ይሆናል ብለዋል።

የ90 ቀናቱ ዕቅዱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተለዩ በሕዝብ የተነሱ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታትና ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።

በከተማዋ ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት፣ የንግድ ሥርዓቱን የመግራትና ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን የመቆጣጠር ሥራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ብለዋል፡፡

የግብይት ሰንሰለቱን ለማዘመንና ምርቶችን በቀላሉ ለነዋሪው ተደራሽ ለማድረግ በየክፍለ ከተማው የሚገነቡ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን ግንባታ ማፋጠንና ለአገልግሎት ማብቃት የዕቅዱ አካል ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሆኑ የማምረቻ ሼዶችን ማብዛት፣ የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በአዲስ ቅኝትና አቅም የመምራት ሥራም ሌላኛው አበይት ተግባር ነው።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በከተማዋ በተገነቡ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት እና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የግብርና እና የኢዱስትሪ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በዚህም አስተዳደሩ ነዋሪው ምርቶችን ከመደበኛው ገበያ እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዲያገኝ በማስቻል የዋጋ ማረጋጋት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

የምርት አቅርቦትን ማሻሻልና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ ከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የግብይት ስርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር ማምጣትም የ90 ቀናት አበይት ክንውን ይሆናል።

ለነዚህ ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚሆን የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን ከማጠናከር ባለፈ የ2018 በጀት ዓመትን በስኬት በማጠቃለልና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ዝግጅትን በልዩ ክትትልና ድጋፍ የማከናወን ሥራ በትኩረት እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review