AMN ሰኔ 10/2018

ኢትዮጵያ እና ቻይና የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ መስኮች ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ እያደገ በሚገኘው የኢትዮጵያ እና የቻይና ትብብርና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ሁለቱ ወገኖች በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አስተዳደር፣ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ የቅድሚያ የትኩረት ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32) አስመልክቶ የሚደረጉ የሎጅስቲክስ ዝግጅቶችን መደገፍ በሚቻልበት የትብብር ሁኔታ ላይም መክረዋል።
አምባሳደር ሃደራ አበራ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን አጋርነት ለማስቀጠል ያላትን አቋም እንደምታደንቅ ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።