ምክክሩ በስኬት ተጠናቋል- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም.

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሳምንታት የምክክር ሂደት በኋላ በዛሬው እለት በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በዚህ ታሪካዊ መድረክ 4ሺ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በመሰባሰብ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመካካሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ተመካካሪዎቹ በመጨረሻም ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሄ የሚሆኑ ምክረሃሳቦችን አጠናቅረው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አክለዋል፡፡

በሂደቱ ተመካካሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በቀላሉ እየተግባቡ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ጊዜ ወስደው ጠንከር ያሉ ውይይቶችን እያደረጉ በመጨረሻም በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሂደቱን ሲከታተል ሁሉም የምክክር መድረኮች በመደማማጥ፣ በመከባባር እና በመቻቻል ሲከናወኑ እንደነበር ማረጋገጥ እንደቻለም ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት የተናገሩት፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ልዩነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር በጋራ ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን እድል መፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር አሸናፊና ተሸናፊን የመለየት ሂደት አይደለም ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ይህ ሂደት አንዱ ወገን ተሸንፎ ሌላው ወገን የሚያሸንፍበት ውድድርም አይደለም ብለዋል።

እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገለፃ በዚህ የምክክር ሂደት ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ ተዋውቀዋል፣ ጠንካራ ግንኙነቶችን ፈጥረዋል፣ የተለያዩ አመለካከቶችን አዳምጠዋል፣ እንዲሁም የሀገራችንን ፈተናዎች በተመለከተ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል፤ በመጨረሻም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያሉባትን የሃሳብ ልዩነቶች በምክክር መፍታት መቻሏን ያሳየችበት ታሪካዊ ምእራፍ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review