ምርጫው ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው-አብን

You are currently viewing ምርጫው ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው-አብን

AMN- ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ትናንት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ሂደት ስኬታማነት በመግለጽ፤ ውጤቱን በጸጋ መቀበላቸውን እና በአብላጫ ድምጽ ላሸነፈው ብልጽግና ፓርቲም የመልካም ምኞት መግለጫ እያስተላለፉ ነው።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝባችን ለሰላም ሲባል ውድ ዋጋ ከፍሎ ያሸነፈበት ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ነው ብሏል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ወደ ተሻለ የፖለቲካ እና የማኅበረ-ኢኮኖሚ ምዕራፍ ለመሻገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ውሳኔ መሆኑንም አመላክቷል።

በመግለጫው ፣ የተመዘገበው ስኬት የማህበረሰባችን የአርቆ አሳቢነት ትሩፋት በመሆኑ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባም ነው ብሏል፡፡

ምርጫው ሕዝባችን ፈተናዎችን ተቋቁሞ በታሪክ የሚዘከር የአይበገሬነት ታሪክ የጻፈበት፣ ለዘላቂ ሰላምና እድገት የሚበጅ የፖለቲካ ባህል አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገበት፣ በዋናነት የማኅበረ-ፖለቲካ ግብረ-ገብ እሴቶች ተቃራኒ የሆኑ ጯሂና እኩይ ድምጸቶችን ማሸነፍ የቻለበት፣ ለሰላም ሲባል ዋጋ የመክፈል ቁርጠኝነት የታየበትና ዋጋ የተከፈለበት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

ሕዝብን ማሸነፍ አይቻልምና ድሉ የሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሆኗልም ነው ያለው።

ምርጫው ለውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት መሆኑንም አብን ገልጿል።

ዳያስፖራው ልማቶችንና የሰላም እንቅስቃሴዎችን እንዲደግፍ እንዲሁም ለሀገራዊ መረጋጋት ፋይዳ ከሌላቸው አጀንዳዎች ራሱን እንዲያርቅ አብን ጥሪ አቅርቧል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ላገኘው ብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልካም ምኞቱን ገልጾ፤መጭው ጊዜ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ሁለንተናዊ ምዕራፍ የምናሻግርበት እንዲሆን ገልጿል።

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review