አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

AMN-ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ህገወጥነትን ለመከላከልና የነዋሪዎችን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሳደግ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በከተማዋ ያለውን ስልጣኔ እና ህግ የማክበር ባህል ይበልጥ ለማሳደግ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አብረው ለመስራት ተስማሙ።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በመድረኩ እንደገለጹት ፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከዚህ ቀደም በአስተማሪ ፕሮግራሞች፣ በድራማዎችና በመዝናኛ ስራዎች የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ ለማድረግ በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

አዲስ አበባ ከአለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ያነሱት ዋና አስፈጻሚው ከተማዋን እንደ ጄኔቭ እና ኒውዮርክ ያሉ የሰለጠኑ ማህበረሰቦች መኖሪያ ለማድረግ የደንብ ማስከበር ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሰለሞን አክለውም፣ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት መሰረተ ልማቶች ትርጉም የሚኖራቸው ህገወጥነት ሲወገድና የስነ-አእምሮ ለውጥ ሲመጣ በመሆኑ፣ ሚዲያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የሰለጠነ የሰው ኃይልን ታጥቆ ህግና ደንብን የሚያከብር ስልጡን ማህበረሰብ ለመፍጠር ሌት ተቀን በትብብር መስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፤ የባለስልጣኑ ራዕይ የደንብ መተላለፍ የሌለባት፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ከተማ መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ለማሳካት ሚዲያ ትልቁ መሳሪያቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ጊዜያት ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በተሰራው የተቀናጀ ስራ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ እና አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ተግባር በስኬት መከናወኑን ሻለቃ ዘሪሁን አብራርተዋል።

የደንብ ጥሰት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ83 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና ይህም ውጤት የተገኘው በኦፊሰሮች ስምሪት ብቻ ሳይሆን በሚዲያ ስራው ጭምር መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

ባለስልጣኑ የትውልድ ድምጽ የሆነውንና የህብረተሰቡን ልቦና የሚያዳምጠውን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ቀዳሚ ተመራጭ ማድረጉን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፣ የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠልና በኮሪደር ልማቱ የተገኙ ስኬቶችን ለማጠናከር የመግባቢያ ስምምነቱ የላቀ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review