በመዲናዋ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነፃ በማድረግ ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ነው – የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን

You are currently viewing በመዲናዋ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነፃ በማድረግ ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ነው – የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን

AMN – ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ 79 በመቶ የሚሆኑ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነፃ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለወራት ሲካሄድ የቆየው የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን ማጠቃለያ ፕሮግራም በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ ብዙ ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

በመሆኑም የእድገቱ ሞተር የሆነውን የሰው ኃይል ጤና ከሚያውኩና ሕይወትን ከሚያጨልሙ እንደ ትንባሆ ካሉ መሠል ሱሶች መጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለዜጎች ሰብዓዊ ልማትና ጤና በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ አዲስ አበባን ከትንባሆ ነፃ ለማድረግ የተቀረፁ ኢኒሼቲቮች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውንም ወ/ሮ ሄራን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሙሉእመቤት ታደሠ በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ በሚመሩ የፀረ-ትንባሆ ዘመቻዎች ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ በማሥራት፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመስበር ትርጉም ያለው ለውጥ መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል::

ዶ/ር ሙሉእመቤት በሕብረተሰቡ ዘንድ የመጣውን ለውጥ በማስረጃ ሲያስረዱም፤ በሦስተኛ ወገን በተደረጉ ጥናቶች 79 በመቶ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት ከትንባሆ ጭስ ነፃ ማድረግ መቻሉንና ከዚህ ቀደም 5.3 በመቶ የነበረውን የአጫሾች ቁጥር ወደ 4.6 በመቶ ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጇ አክለውም ሕግ ጥሰው በተገኙ 800 አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉን አንስተው፤ ሕብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በሚያወጧቸው ተለዋዋጭና አደናጋሪ ማስታወቂያዎች ሳይሸወዱ ጤናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review