ፈተና ለምን ያስፈራል የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች የሚያስረዱት እውነት

AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

ወቅቱ ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የፈተና ጊዜ ነው። ፈተና በትምህርት ዓለም የተለመደ የምዘና መሳሪያ ቢሆንም፣ ለብዙ ተማሪዎች ግን የጭንቀት፣ የፍርሃትና የራስ መተማመን መቀነስ ምንጭ ነው። በስነ-ልቦናው ዓለም ይህ ሁኔታ የፈተና ጭንቀት ይባላል።

ታዲያ ተማሪዎች ፈተናን የሚፈሩት ለምንድን ነው? የትምህርት እና የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ ይህ ፍርሃት ከእውቀት እጥረት ባሻገር ከማህበራዊ ግፊት፣ ከወላጆች ተስፋ እና ከአእምሮአችን ውስብስብ አሰራር ጋር የተያያዘ መሆኑን በዚህ ርዕስ ላይ ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጠው “Test Anxiety: Master Your Nerves to Unlock Peak Performance” የተሰኘው መጽሐፍ፣ ያብራራል።

ተማሪዎች ፈተናን የሚፈሩት ለምንድን ነው?

የውድቀት ፍርሃት፡ ብዙ ተማሪዎች ፈተናን እንደ ቀላል ምዘና ሳይሆን፣ እንደ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው መወሰኛ አድርገው ይወስዱታል። ካልተሳካልኝስ? ወይም ወላጆቼን ባሳፍርስ? የሚል ስጋት የጭንቀታቸው ምንጭ ይሆናል።

ከፍተኛ ማህበራዊ ግፊት፡ ውጤት ከቤተሰብ ክብርና ከወደፊት ዕድል ጋር ሲያያዝ፣ ተማሪው የሚፈራው ፈተናውን ሳይሆን የውጤቱን መዘዝ ነው።

የራስ መተማመን እጥረት፡ በራሳቸው ችሎታ ላይ እምነት የሌላቸው ተማሪዎች ለጭንቀት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ያልተሟላ ዝግጅት፡ በመጨረሻ ሰዓት የሚደረግ የችኮላ ጥናትና የጊዜ አጠቃቀም ችግር ለፍርሃት ይዳርጋል።

ሰው ፈተናን እንደ አደጋ ሲመለከተው፣ አዕምሮው የጭንቀት ሆርሞኖችን ይለቃል። ይህም የልብ ምትን በማፋጠን እና ትኩረትን በመበተን፣ ተማሪው ያነበበውን መረጃ እንዳያስታውስ ያደርገዋል።

እንዲያውም፣ ሁልጊዜ አንደኛ መሆን አለብኝ ብለው የሚያስቡ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ሳይቀሩ፣ ከፍተኛ የፈተና ጭንቀት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።

የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ፈተናን በሰላም ለመወጣት የሚከተሉትን ይመክራሉ፤

ፈተና አንድ የትምህርት ምዘና እንጂ የሰውን ዋጋ መለኪያ አይደለም፤ ይህን መረዳት ጫናን ይቀንሳል።

በመጨረሻ ሰዓት የሚደረግ ጥናት ጭንቀትን ያባብሳል፤ ለፈተና ቀደም ብሎ ይዘጋጁ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት ማስታወስን እና ትኩረትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽላል።

አልችልም ከማለት ይልቅ የተዘጋጀሁትን በልበ ሙሉነት እሰራለሁ በማለት ራስን ማበረታት። በፈተና ወቅት ጭንቀት ሲሰማዎት ጥልቅ ትንፋሽ መውሰድ አእምሮን ለማረጋጋት ይረዳል።

መጠነኛ ጭንቀት ለውጤት መነሳሻ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጭንቀቱ ትኩረትን የሚሰርቅ ከሆነ እነዚህን የመፍትሄ መንገዶች በመከተል ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review