ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው ለነዋሪው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል- ቋሚ ኮሚቴው

AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት ዓመታት ተቋማቶቿ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረጓ ለነዋሪው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ስለማስቻሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል።

ቋሚ ኮሚቴው ባለፉት አምስት ዓመታት ለህዝቡ ሲሰጡ የቆዩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች የሚገመገሙበት፣ በመጪዎቹ ጊዜያትም የተሻለ መስራት በሚቻልበት እቅድ ላይ የሚመክርበትን መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ትራንስፖርት፣ ፅዳት፣ እሳትና አደጋን ጨምሮ በበርካታ መስኮች መልካም ውጤት የተመዘገበባቸው ተግባራት ስለመከናወናቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገልፀዋል።

አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ በዘለለ ኢትዮጵያ ለአስተናጋጅነት በተመረጠችበት 32ኛው የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዝግጅቷ የተሳለጠ ይሆን ዘንድም እየተሰራ ስለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል።

በዘርፎቹ የተመዘገቡት ውጤቶች አበረታች ስለመሆናቸው ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአደጋ ምላሽና ቅድመ ጥንቃቄ ክፍተቶች፣ ፅዳትን በቴክኖሎጂ የማገዝ ጉዳይን የመሳሰሉ ቀሪ የቤት ስራን ይጠይቃሉ ያሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተው ከባለጉዳዮቹ ተቋማትም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጪዎቹ ዓመታትም የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶቹን በመቅረፍ የተሻለች አዲስ አበባን ለመፍጠር የበለጠ መስራት እንደሚገባ ኮሚቴው አሳስቧል።

በመቅደስ ደምስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review