የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

AMN ሰኔ 19/2018

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋምን ጀምሮ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣አመራሮችና የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በዚሁ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)፣ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የአመራር አካላትና የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ናቸው አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩት፡፡

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የዓለም የአየር ንብረት መዛባት ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ መጥቷል።

ኢትዮጵያም ይህንን ችግር አስቀድማ በመረዳትና መፍትሔ ለመሻት ውጤታማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመቅረጽ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

ይህ መርሃ-ግብር የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡

ይህንን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል መላው ሕዝብ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ በነቃ ሁኔታ በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ በየዓመቱ የክረምት ወቅት አባላቱንና መላው ሠራተኞቹን በማንቀሳቀስ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን በስፋት ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአለም ደረጃ አስደናቂ ታሪክ እየሠራች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ልማቱ የደን ሽፋኑን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም፣የደን ሽፋንን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የ”አረንጓዴ አሻራ” መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ መተግበር መጀመሯ ይታወሳል።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ እስካሁን ባሉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ የደን፣ የፍራፍሬና የጥላ ችግኞችን ማልማት ያስቻለ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ ያለውን የስነ-ምህዳር ሚዛን ከመጠበቅ ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ለጎረቤት ሀገራትም የችግኝ ስጦታዎችን የምታበረክትበት ትልቅ አህጉራዊ አሻራ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ‘‘ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ሐሳብ እየተከናወነ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review