AMN ሰኔ 21/2018
የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን የሚያስተናግደው የ’eTax’ ሥርዓት በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ እንደሚሸጋገር የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ አብዱረህማን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ቢሮው ባለፉት ሁለት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን አከናውኗል።
በዚህም ግብር ከፋዮች በአካል ሳይመጡ በኢሜል እና በተዘረጋው የኦንላይን ሊንክ ብቻ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የተቀናጀ የልማት ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ተግባር መግባቱን አመልክተዋል።
ይህ አዲስ ዲጂታል አሠራር ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ምቹ አገልግሎት የሚያገኙበት ምኅዳር የፈጠረ ሲሆን፣ የባለቤትነት ስም ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ተገዥነት አገልግሎቶችንም በውስጡ ያካተተ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቢሮው በራሱ አቅም ያለማውን የዕዳ ክትትል ሥርዓት ወደ ተግባር በማስገባቱ፣ በ17ቱም ቅርንጫፎች የሚወሰኑ የዕዳ ውሳኔዎችን በቅርበት ለመከታተልና የሚሰበሰበውን ገቢ በፍጥነት ወደ ካፒታል በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ነው የገለጹት።
የክሊራንስ (የግብር ነፃነቱ ማረጋገጫ) አሰጣጥ ሂደቱን ይበልጥ ግልጽ፣ ቀልጣፋና እምነት የሚጣልበት ለማድረግም ባርኮድ (Barcode) ያለው አዲስ የኦንላይን አሠራር ተግባራዊ መደረጉንም እንዲሁ።
የተዘረጉት እነዚህ የዲጂታል አገልግሎቶች ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን እንዲያሳውቁና እንዲከፍሉ በማስቻላቸው፣ በየወሩ መጨረሻ ላይ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ይታይ የነበረውን ከፍተኛ መጨናነቅና የረጅም ጊዜ ጥበቃ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን አመልክተዋል።
ቢሮው በቀጣዩ በጀት ዓመትም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችን የሚያስተናግደውን የኢቲ ታክስ (eTax) ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል በማሸጋገር፣ ግብር ከፋዮች ካሉበት ሳይንቀሳቀሱ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን እንደሚተገብር መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።