AMN- ሰኔ 21/2018 ዓ.ም
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃ ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 2 ሺህ 882 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የዩኒቨርስቲው ኘሬዝዳንት ተሾመ ነቅዐ ጥበብ(ዶ/ር) የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከሀገሪቱ የትምህርት ስርዐት ጋር በተጣጣመ መልኩ እየሠራና ብቁ ዜጋን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለትምህርት ዘርፉ እድገት የጥናትና ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርስቲው በዚህ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሠው ሀብት ልማት ስምሪትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር)፤ ትምህርት የሀገሪቷ የለውጥ ሞተርነት ቁልፍ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መሠጠቱን ተናግረዋል።
ተመራቂዎች ትልቅ የለውጥ መሣሪያ በእጃችሁ መግባቱን በመረዳት በሙያችሁ ሀገራችሁን በታማኝነት ማገልገል ይኖርባችኋል ያሉት ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ይህ ቀን የስኬታችሁ ጫፍ ሳይሆን ወደ ቀጣይ ሀላፊነት መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኑን አውቃችሁ ለቀጣይ ስኬት ተዘጋጁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፀጋ ታደለ