AMN – ሰኔ 21/2018 ዓ.ም
አውሮፓ በሙቀት ማዕበል እየተናጠች ሲሆን፤ ዛሬ የሙቀት መጠኑ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል።
በፈረንሳይ ታሪክ የመጀመሪያው በሆነው በዚህ የሙቀት ማዕበል በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል።
የፈረንሳይ የሕዝብ ጤና ኤጀንሲ እንደገለጸው፤ ከሙቀት ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ካጡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አረጋውያን ናቸው።
ኤጀንሲው በእንክብካቤ ማዕከላትና በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተጨማሪ የሞት አደጋ ሊከሰት እንደሚችልም ገልጿል።

ሳይንቲስቶች ሰኔ 13 የጀመረው ይህ የሙቀት ማዕበል በአውሮፓ ከተመዘገቡት ሁሉ የከፋው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ይህ አስከፊ ሁኔታ የኃይል ማመንጫዎችን አስተጓጉሏል፣ መሠረተ ልማቶችን ጎድቷል፣ እንዲሁም የጤና ጥበቃ ሥርዓቶችን ከአቅም በላይ ፈትኗል።
ሳይንቲስቶቹ የሙቀት ማዕበሉ የተከሰተው በሰው ሠራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።
የዚህ ሳምንት ከፍተኛው የሌሊት ሙቀት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ100 እጥፍ ይበልጣል።
በዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ወደ ውጭ ሳይወጡ በቤታቸው ለመቆየት ተገደዋል።
ይህ ከፍተኛ ሙቀት የአውሮፓን ወንዞች ጭምር የጎዳ ሲሆን፤ ውኃዎችን በማድረቅና በማሞቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችንና የእርሻ ሥራዎችን ማስተጓጎሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
በወንድማገኝ አሰፋ