AMN- ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
የእንጦጦ- ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የወንዙን ገጽታ ከመቀየሩም በላይ ለከተማዋ ነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ ስፍራ ፈጥሯል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፕሮጀክቱ ምረቃ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ቀበና ወንዝን ከብክለት በማጽዳት እና ዳርቻውን በማልማት ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
በአካባቢው አፈር እና መሬት መሸርሸርን ለመከላከል ወደ 40 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮንሶ እርከን እና የጋቢዮን ስራ እንዲሁም 20 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ መገንባቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም፣ ወደ መድረቅ ተቃርበው የነበሩ ምንጮች ዳግም ህይወት እንዲዘሩ መደረጉን እና ከ50 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለው በአሁኑ ወቅት መጽደቃቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ወንዙን ለመሻገር ነዋሪዎች ይገጥማቸው የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ መልኩ የተገነቡ 21 የእግረኛ ድልድዮች ለህዝብ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ድልድዮች በተለያየ ውበት እና ቅርጽ የተገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ህጻናትና ወጣቶች በአግራሞት የሚጠቀሙባቸው ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
በወንዙ ዳርቻ ይፈስ የነበረውን የቆሻሻ ውሃ በመግታት እና የንጽህና ሁኔታን በማሻሻል፣ ወደ 23 የሚደርሱ ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ አካባቢው አሁን ላይ ለስፖርት ማዘውተሪያነት፣ ለልጆች መጫወቻነት እና ለካፌዎች አገልግሎት የሚውል ውብ ስፍራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ነዋሪዎችም በአካባቢው መጥተው እንዲዝናኑና አካል ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ የጋበዙት ከንቲባዋ፣ “ትላንት የማይመች የነበረው አካባቢ ዛሬ መልካም ጠረን የሚሸተትበት እና የሚታደስበት ሆኗል” ብለዋል።
ለዚህ ስኬት መሳካት ከቀን ሰራተኞች እስከ ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ላደረጉት ትብብር ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ