ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ35 በላይ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ35 በላይ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ካሏት እጅግ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች ባሻገር ተዘርፈውና ጠፍተው የነበሩ ከ35 በላይ ውድ ቅርሶቿን ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ወደ ሐገር ማስመለስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ከተመለሱት ቅርሶች መካከል ታሪካዊቷ የ”ጸሐይ” አውሮፕላን ፣ የቤተክርስቲያን መስቀሎች እና የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፣ ሀገሪቱ ቀደም ሲል ለታሪካዊ ቅርሶቿና ለቤተ መንግስቶቿ የምትሰጠው ትኩረት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ቅርሶችን እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ከማየት ይልቅ “እንደ እዳ” የመመልከት ስህተት እንደነበር አመላክተዋል።

ቅርሶችን ከማስመለስ ባለፈ ነባሮቹን የመጠገን፣ የማደስ እና የጎደሉትን የመገንባት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህም እንደ ላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ አክሱም፣ ፋሲል፣ ጀጎል እና አባ ጅፋር ቤተመንግስት ያሉትን ሰው ሰራሽ ቅርሶች እንዲሁም እንደ ሶፍ ኡመር ዋሻ ያሉ አስደማሚ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በሰፈርና በመንደር ሳይከፋፈሉ የጋራ ሀብት አድርጎ ለማልማት ትልቅ በር ከፍቷል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ወጣቶች በየቦታው በእግር እየተጓዙ የሀገሪቱን የቱሪስት መስህቦች ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራ እያከናወኑ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ይህም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

አሁን ላይ የተጀመረው ዘላቂና አረንጓዴ ልማትን ያካተተ የቱሪዝም መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ታምኖበታል።

በታምራ ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review