የ “ገበታ” ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማቶች በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የ “ገበታ” ፕሮጀክቶችና የኮሪደር ልማቶች በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ማነቆ የነበሩ የመሰረተ ልማት እጥረቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩት የ“ገበታ” ፕሮጀክቶች እና የኮሪደር ልማቶች በሀገሪቱ ከተሞችና የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የቱሪዝም ዘርፉን ሙሉና ማራኪ ለማድረግ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ላይ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

እንደ እንጦጦ ፓርክ (የሳባ ሙዚየምን ጨምሮ)፣ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ሶፍ ኡመር እና ላሊበላ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ደረጃቸውን ጠብቆ ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ቱሪስቶች ቅርሶችንና ተፈጥሮን ጎብኝተው በቂ እረፍትና መስተንግዶ የሚያገኙባቸውን ቦታዎች የመገንባት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የባህር ማዶና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በቀላሉ መንቀሳቀስ እንዲችሉ የመንገድ እና የአየር መሠረተ ልማቶችን የማዘመን ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በተጨማሪም ጎብኝዎች ሳይጓዙ አስቀድመው ስለ ስፍራው በቂ መረጃና ምስል እንዲያገኙ እንዲሁም በቨርችዋል መንገድ ቦታዎችን መያዝ እንዲችሉ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን የመዘርጋት ሥራዎች እንደተሰሩ አመላክተዋል።

ከገበታ ለሸገር ፕሮጀክት አስደናቂ ውጤት በኋላ የቀጠሉት የ“ገበታ ለሀገር” እና “ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች በርካታ ከተሞችን ወደ አዲስ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ምዕራፍ ማሸጋገራቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የ“ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ የአርባምንጭ ሪዞርትም በቅርቡ እንደሚመረቅ ተናግረዋል።

በጎርጎራ፣ በሀይቅ (ደሴ/ኮምቦልቻን የነካካ)፣ በጅማ እና በጅግጅጋ (የሸበሌ ሪዞርት) የተገነቡት ሜጋ ፕሮጀክቶች በዙሪያቸው ያሉትን ከተሞች ገፅታ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በየቦታው የስብሰባ ቱሪዝምን የሚያነቃቁና ሌሎች የቱሪዝም መስኮችን የሚያሳድጉ የስብሰባ አዳራሾችና የኮንቬንሽን ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም አመላክተዋል።

በትራንስፖርት በኩል በሀገሪቱ ትልቅ እመርታ የታየ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ሰባት ተጨማሪ ኤርፖርቶች ተመርቀው ስራ መጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡

ቀሪዎቹም በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩና ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ባሌ፣ ሀይቅ እና ሸበሌ ሪዞርቶች የሚያስገቡ መንገዶች፣ የመብራትና የውሃ መሰረተ ልማቶች መሟላታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ታላቅ ስኬት ሌላኛው ምስጢር በመንግስት፣ በህዝብና በባለሀብት መካከል የተፈጠረው ጠንካራ ቅንጅት መሆኑን በመጥቀስም፣ የግሉ ዘርፍ በቀጥታ በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማዋጣት ረገድ የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review