AMN- ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎችና ወጣቶች ወደ አካባቢው የሚመጡ ቱሪስቶች ተመላልሰው እንዲጎበኙና ከተማዋ የቱሪዝም መናኸሪያነቷ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በከተማዋ የተከናወኑ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የአርባ ምንጭ ሕዝብ ለቱሪስቶች ሊያደርገው ስለሚገባ እንክብካቤና መልካም ስነ-ምግባር ዙሪያ ጠንካራ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ቱሪዝምና ሌብነት አብረው ሊሄዱ እንደማይችሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንድ ቱሪስት ለቀናት በአርባ ምንጭ ውበት ተደስቶ ቆይቶ አንድ ቀን ንብረት ቢጠፋበት ስለ ከተማዋ መልካም ስም ሳይሆን ስለ ሌብነቱ ለዓለም እንደሚያስተጋባ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም መልካም ስማችን እንዳይጠለሽ ወጣቱና ነዋሪው እንደ ፖሊስና የፀጥታ አስከባሪ ሆኖ ሌብነትን በጋራ ሊከላከል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አርባ ምንጭና አካባቢው በፍቅርና በሰላም የሚታወቅ፣ በሌሊትም ጭምር በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት አስተማማኝ ቀጠና በመሆኑ ቱሪስቶች መጥተው የሚተኙ ሳይሆን ተንቀሳቅሰው ገንዘባቸውን እንዲያወጡ የሰላም ጉዳይ ከምንም በላይ ጥንቃቄ ሊደረግበትና ይሄው የከተማዋ መለያ ሀብት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።
“ባለቤት ያለው ከተማ ወይም ቤት አይቆሽሽም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነዋሪው ለከተማዋ የፅዳት እሴት ትኩረት በመስጠት አካባቢውን በንፅህና እንዲጠብቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአጠቃላይ የአርባ ምንጭ ወጣቶችና ነዋሪዎች ቱሪስቶችን በፍቅርና በደስታ በመቀበል፣ ንብረታቸውንና ሰላማቸውን በማስጠበቅ ከተማዋን የቱሪዝም ተመራጭ እንዲያደርጓት አደራ ተጥሎባቸዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
በአስማረ መኮንን