AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም
በመንግስት ከተቀመጠው ወጥ የቤት ኪራይ ውል ውጪ በጎንዮሽ የሚደረጉ ማናቸውም ስምምነቶች በህግ እንደሚያስጠይቁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስጠነቀቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ከአከራይና ተከራይ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
ኃላፊዋ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ የሚደረገው የቤት ኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ጥናት ፍጹም በህጋዊው ውል ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ ከህግ ውጪ የሚደረጉ ማናቸውም የጎንዮሽ ውሎች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡

በመሆኑም ህግ ጥሰው በሚገኙ አካላት ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃና ተጠያቂነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።
አዲሱ የቤት ኪራይ መጠን የተወሰነው በዘፈቀደ እንዳልሆነ የገለጹት ወ/ሮ ቅድስት፤ የህዝብ ብዛትን፣ የዜጎችን የመክፈል አቅምና ያለውን የቤት አቅርቦት መሰረት ባደረገ ሳይንሳዊ ጥናት መሆኑን አመላክተዋል።
አከራዮች በዘፈቀደ ዋጋ መጫን የማይችሉበት እንዲሁም ደላሎች ተከራዮችን በየጊዜው እያቀያየሩ በመሃል የሚያተርፉበት ያልተገባ አሠራር መቀረፉን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ማዕከላት የውል ማደስ ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ኃላፊዋ አክለው ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው