AMN- ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጳጉሜን 4 የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርተዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ “በኅብር ቀን” ሀገር በቀል እሴቶቻችንን በተግባር በመጠቀም አብሮነትን፣ መረዳዳትንና ሰው ተኮር ተግባራትን ባህል እያደረግን ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር በሁሉም ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞች እና በማዕከል ለከተማችን ነዋሪዎች ማዕድ አጋርተናል ብለዋል፡፡
ሁልጊዜ እንደምናደርገው ጧሪ ደጋፊ ለሌላቸው፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰራተኞችን ጨምሮ ከለውጡ ዘመን ጀምረን እርስ በእርስ በመረዳዳት ያለው ለሌለው እንዲያካፍል በማድረግ ማዕድ እናጋራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ክረምቱን ሙሉ እና በበዓላት ስናጋራ እንደነበረው ሁሉ የማዕድ ብቻ ሳይሆን አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ፍቅራችንን፣ አብሮነታችንን እና አክብሮታችንን ለከተማችን ነዋሪዎች አጋርተናልም ነው ያሉት።

ከንቲባዋ አክለውም፤ አዲሱ አመት የፍቅር፣ የሰላም፣ በትጋት ሰርተን የምንለወጥበት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
መስጠት አያጎድልም ብለው በከተማችን በሙሉ የምናደርገውን የማዕድ ማጋራት ካላቸው አካፍለው አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለሃብቶች፣ ማህበራት፣ ልበቀናዎች ፈጣሪ አምላክ አብዝቶ ይስጣችሁ፤ ከልብ እናመሰግናለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡