የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ

AMN – ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

በበዓሉ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የኃይል መቆራረጦችን ለመቀነስና ድንገተኛ ጥገናዎችን በፍጥነት ለማከናወን የሚያስችል ሰፊ የቅድመ-ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

ተቋሙ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመቀናጀት በመላው አገሪቱ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ትግበራ ገብቷል።

ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ የሚያጋጥሙ ድንገተኛ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት የቴክኒክ ቡድኖች በከፍተኛ ዝግጁነት ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

በአዲስ አበባና በሪጅን ማዕከላት የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በበዓሉ ዋዜማ እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ ክፍት የሚሆኑ ሲሆን፣ በበዓሉ ዕለትም በተመረጡ ማዕከላት ክፍያና ሌሎች አገልግሎቶች ይሰጣሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ፍላጎትን ለማመጣጠን ደንበኞች ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

በተለይም ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባለው የከፍተኛ ፍጆታ ጊዜ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ዕቃዎችን አጠቃቀም መቀነስ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገልጿል።

በበዓሉ ወቅት ማንኛውም የኤሌክትሪክ አደጋ ሲያጋጥም በነፃ የስልክ መስመር 905 በመደወል ወይም በተቋሙ የዲጂታል አማራጮች በኩል ማሳወቅ እንደሚቻል አገልግሎቱ ጠቁሟል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review