ፈርዖኖቹን ለዘመናት የመከቱ ብርቱ ክንዶች

AMN – ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

ግብጽ የአባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ጽኑ ፍላጎት አላት፡፡ቢሆንም ግን አባይን በፍትሃዊ የዉሃ አጠቃቀም መርህ በጋራ እንጂ በብቸኝነት የመጠቀም ተፈጥሯዊም ሆነ ታሪካዊ እንዲሁም ህጋዊ መብት የላትም፡፡

ግብጽ የአባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን እውን ለማድረግ ለረጅም ዘመናት የተለያዩ ህገወጥ ስልቶችን ስትጠቀም ኖራለች፡፡

ግብጽ ኢትዮጵያን አዳክማና አፈራርሳ ታላቋን ግብጽ ለመገንባት ላለፉት በርካታ አመታት ታሪክ ይቅር የማይላቸውን የተለያዩ ሴራዎችንና ደባዎችን በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊያን ላይ ስትፈጽም ኖራለች፡፡

ኢትዮጵያም ተፈጥሮ በቸረቻት የአባይ ውሃ ምክንያት በግብጾች ሴራ የተለያዩ አህጉርና አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ስታስተናግድ ኖራለች፡፡

ግብጾች ከፖለቲካ አልፈዉ ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ሃሰተኛና የፈጠራ ትርክቶችን በመፈብረክ ኢትዮጵያዊያን አንድነትና ህብረት እንዳይኖራቸው፤ እንዲከፋፈሉ እና በሃገራቸውና በመንግስታቸው ላይ አመኔታ እንዲያጡ በርካታ ሴራዎችን ፈጽመዋል፡፡

የሃገርና የወገን ክብር የሌላቸው፣ ከባህላቸው፣ ከሃይማኖታቸውና ከሞራላዊ ሚዛን ያፈነገጡና እና የግል ጥቅማቸውን ያስቀደሙ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያንም ለግብጾች ተቀጥረው የገዛ ሃገራቸውንና ወገናቸውን ሲያቆስሉና ሲያደሙ ኖረዋል፡፡

ግብጽ የኤርትራ ተገንጣይ ኃይሎችን በመደገፍ ፣ ኢትዮጵያን የባህር በር ያሳጣችው እና ሻዕቢያን አስታጥቃ ኢትዮጵያን እንዲወጋ ያደረገችው ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፈራረስ እቅዷን እውን ለማድረግ መሆኑንም ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ህገወጡ የህወሃት ቡድን ከአባቱና ከአያቱ ሻዕቢያ ጎን ተሰልፎ የትግራይ ክልልን እያመሰና ለጦርነት እየተዘጋጀ የሚገኘው ይህንኑ የግብጾችን ሃገር የማፈራረስና የማዳከም ተልዕኮ ለማሳካት እንጂ የደረሰበት የተለየ በደል ስላለም አይደለም፡፡

ሻዕቢያና ህገወጡ የህወሃት ቡድንን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂ ሃይሎች የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የሚያደናቅፉበት ዋንኛው ምስጢር የግብጽን ፍላጎትና የግል ምኞታቸውን ለማሟላት እንጂ ከገዛ ሃገራቸዉና ወገናቸው የሚበልጥባቸው እንዲሁም በንግግርና በምክክር የማይፈታ የተለየ ችግር ስላለም አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ የግብጾችን የዘመናት ጫና ተቋቁማ ፣ ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በመላው ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ዛሬ ላይ ከመድረሷም በላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገንብታ ከራሷ አልፋ ለቀጣናው ብርሃን ሆናለች፡፡

በግብጾች ሴራ ፣ በሻዕቢያና በህገወጡ የህወሃት ቡድን ያጣችውን የባህር በር ለማግኘትም ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review