AMN ሐምሌ 23/2018

የኢትዮጵያና ኬንያ የሁለትዮሽ ትብብር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኃይልና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ መሆኑን የኬንያ የውጭና የዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትርና የካቢኔው ዋና ጸሐፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ገለጹ።
ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያና ኬንያ በመልካም ጉርብት፣ በመተማመንና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ረጅም ዘመናት የዘለቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በየጊዜው እየጠናከረ በመምጣቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኃይል ትስስርና በቀጣናዊ መሠረተ ልማት ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ላፕሴት ኮሪደር ፕሮጀክትም ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በወደብ፣ በመንገድ፣ በባቡር ሀዲድና በሌሎች መሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማፋጠን የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ኬንያ የላሙን ወደብ በማስፋፋትና ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን ከወደቡ ጋር የሚያገናኙ ኮሪደሮችን በማልማት ለኢትዮጵያ አማራጭን ለማስፋት እየሰራች መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያና የኬንያ የኃይል ትስስርም የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር ዋነኛ ማሳያ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት የተፈራረመችው ስምምነትና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተገነቡት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የቀጣናዊ የኃይል ትስስርን እያጠናከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ያደረገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የፖለቲካ መተማመንና የኢኮኖሚ ትብብር እየጠነከረ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በመልካም ጉርብት፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ውህደት ላይ የተመሰረተውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በቀጣይም የበለጠ በማጠናከር ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦችና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ብልፅግናና ዘላቂ ልማት በቅርበት እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
S