አላማ ቢሱ – የተሳለዉ መጥረቢያ

AMN – ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

ህገወጡ የህወሓት ቡድን በአንድ በኩል ለህገ መንግሥቱና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተገዢ መሆንን አልመረጠም።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሻዕቢያ እና ግብጽ ካሉ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን በመሰለፍ የገዛ ሀገሩን ለመውጋት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ይህ ቡድን አፍሪካን ጨምሮ መላው ዓለም ያደነቀውን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ እና የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይል በማፍረስ፣ ሕዝቡን ለጦርነት በማዘጋጀት ላይ የሚገኝ የክፍለ ዘመናችን የኋላ ቀር ፖለቲከኞችና አዛውንቶች ስብስብ ነው።

ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ዛሬ ላይ በትግራይ ክልል ወጣቶችን በማፈን ለጦርነት ያዘጋጃል፤ ወደ ሱዳን አሳልፎ ይሸጣል፤ ሕዝቡን ለጦርነት ይቀሰቅሳል፤ የትግራይን ሕዝብ ከገዛ ወንድሞቹና እህቶቹ ለመነጠል የቡድኑ ልሳን በሆኑ መገናኛ ብዙኃንና ተቀላቢ አክቲቪስቶች አማካኝነት ሐሰተኛና የጥላቻ ንግግሮችን ያሰራጫል።

የትግራይ ሕዝብ ዋንኛ የሰላምና የጸጥታ ሥጋት ራሱ ህገ-ወጡ ቡድኑ ሆኖ ሳለ፣ ለዘመናት በሚጠቀማቸው ሐሰተኛ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ የህልውና አደጋ ተጋርጧል በማለት የአዞ እንባ ያነባል።

የትግራይ ወጣቶች አፈና፣ አፈሳና ጦርነትን ጠልተው ክልሉን ለቀው በመሰደድ ላይ የሚገኙት የትግራዋይ ዋንኛ የሰላምና የጸጥታ ሥጋት በሆነው፣ ከሻዕቢያና ከግብጽ ጎን ተሰልፎ የገዛ ሀገሩን ለመውጋት በሚያሴረው ህገ-ወጥ ቡድን ምክንያት እንጂ በሌላ አካል አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በትግራይ ክልል ካለው ሰው ይልቅ ከክልሉ ውጪ ያለው ትግራዋይ በሰላም እየኖረ ነው ማለታቸውም የክልሉ ዋንኛ የሰላም ሥጋት ራሱ ህገወጥ ቡድን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ከሕዝብ ተነጥሎ፣ ሕዝብን አስለቅሶ፣ ሕዝብን ዘርፎ የሚደረግ ትግል ምንም አይነት ውጤት እንደማያመጣ ከታሪኮቻችን ልንማር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት አብዛኛውን ጉዳይ በትዕግስት የሚያየውና ወደ ግጭት የማይገባው የህገወጥ ቡድኑ የትግል መንስኤ ዓላማ ቢስ ስለሆነ ነው፤ ከህገወጡ ቡድን ጋር በመጋጨት የሚሳካ አንዳችም ነገር ስለሌለ ነዉ ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የፖለቲካ አውድ የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ህገወጡ የህወሓት ቡድን ዋንኛ አካሄድ የሻዕቢያና የሌሎች አካላትን አጀንዳ ከማስፈጸም ውጪ ለራሱም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ የሚያመጣው አንዳችም ለውጥ የለም ሲሉ አጽንኦት ሠጥተዋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

#linkAddis

#addisababa

#Ethiopia

#media

#addismedianetwork

#voiceofgeneration

👇
👇
👇
👇
👇
👇
👇

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review