AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሆለታ በሚገኘው የአካዳሚው ግቢ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ጌታቸው ሀብታሙ፣ የክብር ጄነራል መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ በስልጠናው ብልጫ ያመጡ ዕጩ መኮንኖች በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የማዕረግ ማልበስ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ጌታቸው ሀብታሙ፤ ተመራቂዎቹ የወሰዱት ስልጠና ሁለንተናዊ የአመራር ጥንካሬን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
ዕጩ መኮንኖቹ ከትምህርትና ስልጠናው ያገኙት እውቀት እና ክህሎት ማንኛውምንም የሠራዊት የግዳጅ ተልዕኮ መወጣት የሚያስችል አቅም አጎናፅፏቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ አፍሪካውያን ዕጩ መኮንኖችም ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸውንም ተናግረዋል።