AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ከኢትዮጵያ ፖስታ ጋር በመተባበር የተዘጋጀውና የታተመው ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተከናወነ።
ይህ በጋራ ፕሮጀክትነት የተከናወነው የቴምብር ህትመት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ታሪካዊነት፣ የህዝቡን ተሳትፎ ፣ የትውልዱን አሻራ እንዲሁም የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎትና እንችላለን የሚል መንፈስ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው።
የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወርቁ ጓንጉል እንደገለጹት፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የዘመናችን አድዋ በመሆኑ የዚህን ትውልድ ጥረትና አዲስ ትርክት የሚያሳይ ቴምብር መታተሙና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ መደረጉ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነው።
የኢትዮጵያ ፖስታ ሀገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ሀገርን በማስተዋወቅ ረገድ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ የፊላቴሊ ክፍል ኃላፊ አቶ ኤርምያስ ገብረሚካኤል ፣ ቴምብሩ በዓለም አቀፍ የፖስታ ህብረት በኩል በ192 አባል ሀገራት ሙዚየሞች ውስጥ የሚቀመጥና የሚሰራጭ በመሆኑ የሀገራችንን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ቴምብሩ የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ የተዘጋጀ በመሆኑ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችም ለዓለም ህዝብ ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
በዓለም የፖስታ ህብረት በኩል ለ192 ሀገራት የሚሰራጩት አራት ዓይነት ቴምብሮች የኢትዮጵያን አንድነትና የእድገት ተስፋ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማብሰር ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
የህዳሴን ግድብ ፕሮጀክት በሀገራችን ተገንብቶ ለመጠናቀቁ ማሳያ የተዘጋጀው ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስኬት ለዓለም በማብሰር ረገድ ያለው ሚና ጉልህ እንደሆነም ከፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።