ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምናልመው ሁሉ እውን የሚሆንበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

You are currently viewing ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምናልመው ሁሉ እውን የሚሆንበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገሪቱ ለዘመናት ስታልመው የነበረውን ልምላሜ እውን ያደረገና ያለፈውን የድርቅና የሰቆቃ ታሪክ ለመቀየር ያስቻለ ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ታዬ እንደገለጹት፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ ኢትዮጵያ የምታልመውን ሁሉ እውን የምታደርግበትን አዲስ ዘመን ያበሰረ ነው።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የተቸረች ብትሆንም ቀደም ሲል የነበረው የማልማት ተነሳሽነት አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ለከፍተኛ የአየር ንብረት መዛባት፣ ለድርቅና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋልጣ መቆየቷን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል።

እኛ በደረስንበት እድሜ እንኳን ብዙ ስቃዮችና ሰቆቃዎችን አይተናል፤ ከበረሃማነትና ድርቅ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍለናል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄው ይህንን የድርቅና የሰቆቃ ታሪክ ለመቀየር ከተወጠኑ ታላላቅ ተነሳሽነቶች አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለራሱ፣ ለህይወቱና ለተተኪው ትውልድ ሲል በታላቅ ቁርጠኝነት ችግኝ በመትከል ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ዘንድሮ የታቀደው የ8 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ሀገሪቱንና የህዝቡን ቁርጠኝነት የሚመጥን ታላቅ እቅድ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋትና በይዘቱ መሰል ታላቅ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሚያካሂዱት ጥቂት ሀገራት ብቻ መሆናቸውን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ተግባር በየቀኑ የዓለም ሪከርድን እየያዘ ያለና ሀገሪቱ ሊኖራት የሚገባውን ክብርና ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review