ፋይዳቨርስ በይፋ ሥራ ጀመረ

You are currently viewing ፋይዳቨርስ በይፋ ሥራ ጀመረ

AMN – ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረው ፋይዳቨርስ በይፋ ሥራ መጀመሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም 50 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ከ160 ሚሊየን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶችን በመስጠትና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ የዲጂታል ኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑን አስመስክሯል ብለዋል።

ዛሬ ይህ ስኬት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋግሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ፋይዳቨርስ በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆን ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት፡፡

ይህ ውሳኔ ዲጂታል ማንነት ልክ እንደ መንገድ፣ ኃይል እና ቴሌኮሙኒኬሽን ሁሉ ለሀገሪቱ ተወዳዳሪነትና ዘላቂ እድገት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ መሰረተ ልማት መሆኑን ማረጋገጫችን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

አገልግሎቱ ከሀገር አልፎ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ አህጉር ልምድና አቅም በማጋራት፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ሽግግር መሪ የሚያደርጋት መሆኑንም አመላክተዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬት የሚለካው በደረስንባቸው ቴክኖሎጂዎች ሳይሆን፤ ሕዝባችን እነዚህን ውጤቶች የራሱ አድርጎ ሲጠቀምባቸው እና ሕይወቱ ሲለወጥ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለዚህም የቴክኖሎጂ አቅርቦት ጥራትን በመጠበቅ፣ የዳታ ደኅንነትን በማረጋገጥ እና የዜጎችን ዲጂታል ግንዛቤ በማሳደግ የተያዘው አቅጣጫ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review