በስፖርት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው- ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

You are currently viewing በስፖርት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው- ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

‎AMN- ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም

በስፖርት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀሙን እና የ2019 እቅድ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።

ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በ2018 ዓ.ም በባህል፣ በስፖርት እና በኪነጥበብ ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

ላለፉት 28 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረውን የስፖርት ፖሊሲ ዘመኑን በዋጀና አዳዲስ አሰራሮች ተካተውበት መሻሻሉን አስረድተዋል።

ስፖርትን በህግ፣ በአስተዳደር እና በስርዓት ለመምራትም ለመጀመሪያ ጊዜ የስፖርት ልማትና አስተዳደር አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁን አንስተዋል።

በባህል ዘርፍም የኢትዮጵያውያንን አብሮነት፣ አንድነት እና ወንድማማችነት የሚያጠናክሩ 52 የሚሆኑ በዓላት በስኬት መካሄዳቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ኪን ኢትዮጵያ የባህል ቡድን ሀገራችን ያሏትን ቱባ ባህሎችና እሴቶች በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር የማስተዋወቅ ሥራ መስራቱንም ተናግረዋል፡፡

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ለቀጣይ አመት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጁ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በስፖርት ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም የተከናወኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጉልህ ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ትላልቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በትኩረት እየሰራ መሆኑንና እስካሁንም በ2019 ዓ.ም 4 ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮችን በኢትዮጵያ ለማካሄድ እድል መገኘቱን ተናግረዋል።

በደሳለኝ ሙሐመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review