ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነትና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ዓርማ

AMN – ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መገለጫ፣ የነፃነት አርማ እና የዜግነት ክብር ማሳያ ነው።

ሰንደቅ ዓላማ ከስፋቱና ርዝመቱ ባሻገር፣ አንድ ሕዝብ ታሪኩን፣ ትግሉን፣ ትናንቱንና ዛሬውን አጣምሮ የሚይዝበት እንዲሁም የነገው ትውልድ ራዕዩን የሚያስቀጥልበት ሕያው የማንነት መገለጫ ነው።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ ዛሬ የሚከበር ሲሆን፤ በተለያዩ ሀገራት ባሉ ኤምባሲዎችም ይከበራል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን መታሰቡና በድምቀት መከበሩ በርካታ ሀገራዊ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን፣ ልዩነቶችን በውበት ይዞ፣ በአንድ የጋራ አርማ ጥላ ሥር በሰላም አብሮ ለመኖር ያለውን ቃልኪዳን ያድሳል።

ወጣቱ ትውልድ ሰንደቅ ዓላማ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን፣ በብዙ መስዋዕትነት ተጠብቆ የቆየ መሆኑን ተገንዝቦ የሀገር ፍቅር ስሜቱ እንዲጎለብትም ያደርጋል።

ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ለጋራ ከፍታና ለሰላም ዘብ ለመቆም የማንቂያ ደወል ይሆናል።

ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ማለት የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ክብር ማስቀደም ማለት ነው።

ዜጎች ለሰንደቅ ዓላማቸው ሊሰጡ የሚገባቸው ፍቅርና ክብር በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሊገለጽ ይገባል።

ዜጎች በታማኝነትና ለሀገር እድገት በመትጋት፣ የሰንደቅ ዓላማውን ከፍታና ክብር በየትኛውም የሥራ መስክ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ በኩራት ማስቀጠል ይገባቸዋል።

የሰንደቅ ዓላማውን ሕጎችና ደንቦች በማክበር በሰንደቅ ዓላማ ሥር የተገባውን የሰላምና የኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ቃልኪዳን በተግባር መግለጽ ትልቁ የዜግነት ድርሻ ነው።

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬዉ ዕለት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚከበር ይሆናል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review