ለሀገራቸው ሰንደቅ የተዋደቁ አትሌቶች

AMN-ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የሀገር ሰንደቅ አላማን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ስፖርት አቻ አይገኝለትም። በታላላቅ የስፖርት መድረኮች መካፈል ሀገርን ለዓለም ለማሳወቅ ትልቅ መሰረት አለው። ኢትዮጵያ በዚህ ታድላለች። በተለይ በሩጫው ስሟ ደጋግሞ ተነስቷል። ሰንደቋ ለዓለም ተዋውቋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አብዝተው የሚዘወተሩት እግርኳስ እና አትሌቲክስ መሰረት እንዲይዙ አሻራ ማስቀመጥ ችላለች። በአትሌቲክስ ብርቅዬ አትሌቶቿ በአለም አደባባይ ያመጧቸው የከዚህ ቀደም ድሎች ከኢትዮጵያ አልፈው አህጉሪቱን ቀዳሚ አድርገዋል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ለጤንነቱ ሳይሰስት ማራቶንን በባዶ እግሩ ሮጦ ድል ሲያደርግ የተነሳችው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም። ድሉ ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን ፈር ቀዳጅ ስለነበር የአህጉሪቱም ስም ደግሞ ደጋግሞ ተነስቷል። ሻምበል አበበ ቢቂላ በፅናት እና በወኔ ተፋልሞ እስካሁን ድረስ ማንም ያላደረገውን ማራቶንን በባዶ እግር የሮጠው ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ሲልም ነው። ወታደር እንደመሆኑ የሰንደቅን ትርጉም በደንብ የተረዳ ነበር። በባዶ እግር መሮጥ ተራ ነገር ነው። እርሱ ለሀገሩ ሰንደቅ ሕይወቱን ለመስጠት የማይሳሳ ብርቱ ጀግና ነበር።

ፋጡማ ሮባም ገድሏ ሊዘከርላት የሚገባ አትሌት ናት። እአአ 1996 በአታላንታ ኦሎምፒክ ያስመዘገበችው የማራቶን ድል የኢትዮጵያን ሰንድቅ አላማ በዩናይትድ ስቴት አሜሪካ ምድር ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጓል።

ሀገሯን በኩራት ያስጠራችው ፋጡማ ከ30 ዓመት በፊት ያገኘችው ድሏ በርቀቱ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ተብሎ ተመዝግቧል። በማራቶን ታሪክ በሴት አትሌት የተገኘ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ተብሎም በታሪክ መዝገብ ተሰንዶ ቁጭ ብሏል። ፋጡማ ሀገርን እንዴት በድል ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየች ብርቱ ናት። ድሏም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ አሳይቷል።

ደራርቱ ቱሉ ሌላኛዋ የሀገር እና የአህጉር ብርሃን ናት። እኤአ 1992 የባርሴሎና ኦሎምፒክ ተካፍላ በ10ሺ ሜትር ያመጣችው ወርቅ ዘላለም የሚዘከር ታሪክ የተፃፈበት ነው።

በኦሎምፒክ የመጀመሪያውን ወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ጥቁር አፍሪካዊት የሚለው ማዕረግ ለደራርቱም ለኢትዮጵያም ብሎም ለአፍሪካም በኩራት የሚነገር ድንቅ ታሪክ ሆኗል። ረዳት ኮምሽነር ደራርቱ ቱሉ ለሀገር ሰንደቃላማ መዋደቅ ትልቅ ክብር መሆኑን ባለማመታት ሁሌም ባገኘችው አጋጣሚ ትናገራለች።

በሞያዋም በተግባር አሳይታለች። ድል አድርጋ የሀገሯ ሰንደቅ ሲሰቀል ስታይ አምብታለች።ሀገሯን ከፍታው ላይ በማስቀመጧ የደስታዋን ጥግ በእንባ ገልፃለች። ሰንደቁን ስታይ የተፈጠረባት ያ ስሜት ሌሎችም ላይ ይጋባል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን ስታይ የተሰማት ድካሟ አይደለም ፤ ላቧን አፍሳ ያመጣችው ድል ሀገሯን ቀዳሚ በማድረጉ የተሰማት ጀግንነት ነው።

ሀይሌ ገ/ስላሴ ሀገር መውደድን ሰንደቋን ማክበርን ምንኛ ኩራት እንዳለው ደጋግሞ ተናግሯል። እርሱ ሀገሩን አክብሮ አስከብሯታል። በወርቃማ እግሮቹ እየተስፈነጠረ ቀዳሚነቱን በተደጋጋሚ ለማንም ሳያስነካ ሰንደቋን ከፍ አድርጓል።

ድሉን እንዳረጋገጠ የሀገሩን ሰንደቅ ይፈልጋል። የሮጠው ለእርሱ ነው። ሰንደቁን ካልያዘ ባዶነት ይሰማዋል። ከማንም በላይ ልቆ ለመገኘት ልምምድ የሰራው በውድድሩም ያለውን አቅሙን ሁሉ የሰጠው ለሰንደቁ ክብር ሲል ነው።

ሀይሌ ገ/ስላሴ ሀገሩን ቀዳሚ ያደረገው ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ብቻ አይደለም። እኤአ በ2000 የሲድኒ ኦሎምፒክ 10ሺ ሜትሩን የተወዳደረው የእግር ጣት ጉዳት እያለበት ነበር። ይህን ያደረገው ለሀገሩ ክብር ሲል ነው።

ከኬንያዊው አትሌት ፖል ቴርጋት ጋ ተናንቆ ወርቅ ያመጣው በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ሀገሩ አሸናፊ እንድትሆን ካለው ምኞት ነው። ሰንደቋ በብሔራዊ መዝሙሯ ታጅቦ ሲሰቀል ከማየት የበለጠ ደስታ ለሀይሌ ከየትም ሊገኝ አይችልም።

ለዚህም ነው በ1996ቱ የአትላንታ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያውን አግኝቶ ሰንደቅ አላማው ሲሰቀል ፈቅሎ የወጣው የደስታ እንባ ከቁጥጥር ውጪ የሆነበት። እርሱ እንደዚህ ነው በተሰማራበት በሌላ መስክም ቢሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ ለማሳየት የሚጥር።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት አትሌቶች ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብር ናቸው። ለሌሎች አትሌቶችም በር ከፋች የሆኑ። ሀገርን የማክበር ደረጃውን አሳይተዋል። ተከታዮቹም ሃላፊነቱን በሚገባ ተቀብለዋል። ቀነኒሳ በቀለ ፣ ጥሩነሽ ዲባባ ፣ መሰረት ደፋር እንዲሁም ሌሎች ሀገር ሁሌም የምትዘክራቸው አትሌቶች የኢትዮጵያን ከፍታ አስቀጥለዋል።

በየውድድሩ የሀገራቸውን ሰንደቅ በድላቸው ደጋግመው አሳይተዋል። አሁንም የሀገራቸውን ሰንደቃላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እያደረጉ የሚገኙ አትሌቶች በርካታ ናቸው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review