ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በመተጋገዝ ፣ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አንድነት ዱዓ በማድረግ ሊሆን ይገባል

You are currently viewing ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በመተጋገዝ ፣ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አንድነት ዱዓ በማድረግ ሊሆን ይገባል

AMN – ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም

ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የነብዩን (ሶ.ዐ.ወ) አስተምህሮ እና የህይወት ፈለግ በመከተል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማገዝና ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት ዱዓ በማድረግ እንዲሆን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ በዓልን በተመለከተ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጫ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫውም፤ ለመላው ህዝበ ሙስሊም እንኳን ለ1 ሺህ 501ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ ሲል ምክር ቤቱ መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ እንደገለጸው፤ መውሊድ ታላቁ ነብዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) በአላህ ፈቃድ የተወለዱበት ቀን የሚዘክርበት ዕለት ሲሆን ዕለቱ ለዓለማት እዝነት የተላኩት ነብዩ ሙሀመድ ዘመን አይሽሬ ነቢያዊ ተልዕኳቸውን፣ አስተምህሯቸውን እና ሰብዓዊ አርአያነታቸውን የምናስተነትንበት ልዩ አጋጣሚ ነው።

በእርሳቸው መወለድ የሰው ልጆች ያገኙትን መለኮታዊ የብርሃን ብስራት እያወሳን ከልብ የምንደሰትበት፣ ስማቸውን ደጋግመን በመጥራት የአላህ ውዴታ እና ሰላምታ የምናቀርብበትም ነው ሲል ምክር ቤቱ አንስቷል።

በታላቁ ነብይ (ሶ.ዐ.ወ) ላይ የተወረደው መለኮታዊ መመሪያ (ቁርኣን) በተግባር የተኖረው የሕይወት ፈለጋቸው እና አስተምህሯቸው ለመላው የሰው ልጅ መሪ ብርሃን ሆኖ በማገልገል ላይ እንደሚገኝም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የነብዩን (ሶ.ዐ.ወ) አስተምህሮ እና የህይወት ፈለግ በመከተል አቅመ-ደካሞችን፣ ተፈናቃዮችን በአጠቃላይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማገዝና ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት ዱዓ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ ይቅር መባባል ኢስላማዊ እሴትች መሆናቸውን በመረዳት ሀገራዊና ውስጣዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚገባም ምክር ቤቱ በመግለጫቸው ጠቁሟል፡፡

ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውጤታማ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ህዝበ ሙስሊሙ አዎንታዊ ድጋፍ እና ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል “የፍትሁ ነብይ” በሚል መሪ ሀሳብ የፊታችን ማክሰኞ ይከበራል፡፡

በአንዋር አሕመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review