የምላስ መሰንጠቅ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መፍትሔዎች

You are currently viewing የምላስ መሰንጠቅ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መፍትሔዎች
  • Post category:ጤና

AMN- ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም

የምላስ መሰንጠቅ በአብዛኛው ሰዎች ላይ የሚታይ ሁኔታ ሲሆን፣ በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት የጤና ችግር አይፈጥርም።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል።

በየካቲት 12 ሆስፒታል የአንገት በላይ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ኦልያድ ታረቀኝ፣ ስለ ምላስ መሰንጠቅ የሰጡት ማብራሪያ የምላስ መሰንጠቅ በአብዛኛው ሰዎች ላይ የሚታይ ሁኔታ ሲሆን፣ በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት የጤና ችግር አይፈጥርም።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር ተያይዞ ሊከሰት ሚችለውን ችግር አብራርተዋል፡፡

የምላስ መሰንጠቅ ትክክለኛ መንስኤ በብዙ ሁኔታዎች እንደማይታወቅ የገለጹት ዶክተር ኦሊያድ፣ ሆኖም በተለይ የቫይታሚን ቢ12 እጥረት በምላስ ላይ ያሉ ጣዕም ለይተው የሚያሳዩ ክፍሎች እንዳያድጉ በማድረግ ምላስ እንዲሰነጣጠቅ ያደርጋል ብለዋል።

የፎሊክ አሲድ እጥረት እና “ፐርኒሸስ አኒሚያ” የተባሉ የደም ማነስ ዓይነቶች ምልክት ሆኖ የምላስ መድረቅ እና መሰንጠቅ ሊከሰት ይችላል።

የአይን፣ የእንባ እና የአፍ ውስጥ የምራቅ እጢዎችን የሚያደርቀው “ሾግረን ሲንድረም” የተባለ በሽታ የምላስ መሰንጠቅን ሊያስከትል ይችላል። በአንዳንድ ሰዎች ላይ ምንም ዓይነት በሽታ ሳይኖር በተፈጥሮ የሚከሰት የምላስ መሰንጠቅም ሊኖር ይችላል ብለዋል።

ምላስ መሰንጠቅ ብቻውን በሽታ አይደለም የሚሉት ዶክተሩ፣ ነገር ግን በምላስ ስንጥቃት መካከል የምግብ ቅንጣቶች መከማቸት፣ የፈንገስ በሽታዎች መራባት፣ በምላስ ላይ የማቃጠል ስሜት መሰማት፣ የጣዕም መለየት ችግር፣ የአፍ ጠረን መቀየር፣ ምልክቶች ሲታከሉ እንደ ጤና ችግር ይታያል ብለዋል፡፡

ሕክምና እና መከላከያ መንገዶች

የምላስ መሰንጠቅን ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀድሞው መመለስ ሁልጊዜ አይቻልም። ሆኖም፤የአፍ ንጽህናን መጠበቅ፡ ምላስን በደንብ ማጽዳት እና የታዘዙ የአፍ መጉመጥመጪያ ፈሳሾችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ዶክተር ኦሊያድ ይናገራሉ።

ይህ በምላስ ስንጥቃት ውስጥ የሚቀሩ ምግቦች እንዳይበሰብሱ እና የፈንገስ ኢንፌክሽን እንዳይከሰት ይከላከላል፡፡ የጤና እክሎችን ማከም፡ እንደ ቫይታሚን እጥረት ወይም የደም ማነስ ያሉ መሰረታዊ የጤና ችግሮች ካሉ፣ እነሱን ማከም ምላስ ወደ ተፈጥሯዊ ሁኔታው እንዲመለስ ይረዳል።

የምላስ መሰንጠቅ ችግር ካለብዎ፣ ከባድ ችግር ከመከሰቱ በፊት የጥርስ ወይም የአፍ ጤና ባለሙያን በማማከር ተገቢውን የአፍ ንጽህና አጠባበቅ መንገድ መለየት እንደሚገባ በመግለጽ፣ እነዚህ እርምጃዎች ችግሩን ለመቆጣጠር እንደሚረዱ አስገንዝበዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review