AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፣ ይህም በዘርፉ እየተሠራ ያለው ስራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
በ2018 ሀገር አቀፍ በአጠቃላይ ፈተናውን ለመውሠድ ከተመዘገቡ 563 ሺህ 960 ተማሪዎች 550 ሺህ 210ሩ ፈተናውን መውሠዳቸው ተጠቁሟል።
ከእነዚህም ውስጥ 70 ሺህ 544ቱ ተማሪዎች ብቻ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ነው የተገለጸው።
አዲስ አበባ 32.34 በመቶ ወይም 18ሺህ 646 ተማሪዎች ማለፍ የቻሉ ሲሆን፣ በሁሉም ክልሎች የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ከአምናው የተሻለ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
88 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን ማሳለፋቸውንም ገልጸዋል።
ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርትቤቶች 565 ሲሆኑ፣ አምና ከነበረው 1 ሺህ 232 ዘንድሮ በግማሽ ያህል መቀነሱንም አመላክተዋል።
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ከፍተኛው ውጤት 591.6 በመሆን ሲመዘገብ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 576.25 ሆኖ ተመዝግቧል።
የተማሪዎች ውጤትም በመጪው ሰኞ ይፋ የሚደረግ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በፀጋ ታደለ