ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት እንደሚቻል ተግባራዊ ልምድ እንድናገኝ እድል ሰጥቶን አልፏል-ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

AMN – ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርን መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ፓርቲው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርን መጠናቀቅ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

በምክክር ሀገር ትዳን!!

መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለረዢም ጊዜ የቆዩ የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ታስቦ ከአራት ዓመታት በላይ ዝግጅት ሲካሄድበት የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀምሌ 8፣ 2018 ተጀምሮ ከትናንት በስቲያ ነሀሴ 16 ተጠናቋል።

በምክክሩ ከመላ የሀገራችን አካባቢዎች የተወከሉ ተመካካሪዎች ተሳትፈዋል።

በምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የኃይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ ተወካዮች፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የክልል እና የፌዴራል መንግስት ተወካዮች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ተቋማት ተሳትፈዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች በስምንት ዋና ዋና ክፍሎች በተደራጁ አጀንዳዎች እና በበርካታ ንኡስ አጀንዳዎች ዙሪያ ከአንድ ወር በላይ ለዘለቀ ጊዜ ጥልቅ ውይይት አካሂደው ምክረ ሀሳቦችን አቅርበዋል።

በተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር በበርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል። ከዚህ አንጻር በፖለቲካ እና በሀገር ግንባታ የውይይት ዘርፎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት እና አሰራር፣ የምርጫ ስርዓት፣ የመንግስት ቅርጽ እና አደረጃጀት፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ ስርዓት፣ የፌዴራል ስርአት አወቃቀር፣ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ግንኙነት፣ የመንግስት የስራ ቋንቋ፣ የማንነት ጥያቄዎች እና የአስተዳደር ወሰን፣ ሀገራዊ ምልክቶች፣ የቦታ ስያሜ እና ቅርስ አጠባበቅ፣ የጸጥታ ተቋማት አደረጃጀት እና አስተዳደር እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።

በተመሳሳይ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ተቋማት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደር አጀንዳዎች ዙሪያ የኃይማኖት እና የአምልኮ መብቶች አከባበር፣ የመሬት ስሪት፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ክፍፍል፣ የግብር ስርዓት፣ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ፣ የከተሞች አስተዳደር፣ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ሚና፣ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ፣ የተቋማት ገለልተኝነት፣ የግጭት መንሴዎች እና የሰላም ግንባታ፣ ጣምራ ዜግነት፣ የሽግግር ፍትህ፣ አካታች የፐብሊክ ሰርቪስ እና ተያያዥ አጀንዳዎች ዙሪያ በርካታ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።

በሁሉም የምክክር አጀንዳዎች ዙሪያ የተደረጉ ጥልቅ ውይይቶች የተለያየ ማንነት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ፍላጎት ባላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል የተሻለ የሀሳብ መቀራረብ እንዲፈጠር፤ አንዱ የህብረተሰብ ክፍል የሌሎችን ሀሳብ፣ ህመም፣ ስጋት እና ተስፋ መረዳት እንዲችል እድል ፈጥሯል።

በተመሳሳይ በተለያዩ መስኮች ሀገራችን ካሉባት ችግሮች መላቀቅ ትችል ዘንድ፣ በቀጣይ ለሚወጡ ህጎች እና ፖሊሲዎች መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።

ከሁሉም በላይ የተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የትኛውንም ዓይነት የሀሳብ ወይም የአመለካከት ልዩነት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስቦ በንግግር፣ በውይይት እና በድርድር መፍታት እንደሚቻል ተጨባጭ እና ተግባራዊ ልምድ እንድናገኝ እድል ሰጥቶን አልፏል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን በሊሂቃን እንዲሁም በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚታዩ የሀሳብ ልዩነቶች ሊታረቁ የሚችሉት ሁሉን በሚያሳትፍ ሀገራዊ ምክክር ነው ብሎ በጽኑ ያምናል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን የእርስ በእስር ጦርነት ሊቆም እና ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው በሀገራዊ ምክክር እንደሆነ ይገነዘባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሊፈታ የሚችለው፣ ሀገራችን ከድህነት አዙሪት ተላቃ እና ልማትን ማረጋገጥ ዜጎቿ ከስደት፣ ከርሀብ እና ከእርዛት መታደግ የምትችለው በምክክር ብቻ ነው የሚል ጠንካራ የፖለቲካ እምነት አለው።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ለሀገራዊ ምክክር ካለው እይታ በመነሳት ላለፉት በርካታ አመታት ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ለመንግስት እና ለሌሎች አካላት ተከታታይ ጥሪዎችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ ከማድረግ ባሻገር ለሂደቱ መጀመር እና መሳካት አስተዋጾ ያደርጋሉ ያላቸውን ሰነዶች እና የስልጠና ማንዋሎች በማዘጋጀት ለአባላቱ እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት አጋርቷል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራዊ ምክክሩ የነበረውን ተሳትፎ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ምክረ ሀሳቦችን የያዘ “የነእፓ የሀገራዊ ምክክር ሰነድ” አዘጋጅቶ በዚሁ እየተመራ በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለሀገራዊ ምክክር ከሚሰጠው ከፍተኛ ዋጋ እና ለምክክሩ ካደረገው ሰፊ ዝግጅት በመነሳት፣ በሀገራችን የመጀመሪያው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መጠናቀቁ አንድ ታሪካዊ የፖለቲካ ሂደት አድርጎ ይወስዳል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዝግጅት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአራት አመት በላይ በርካቶች በሂደቱ በመሳተፍ አስተዋጾ አበርክተዋል።የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነትን አጉልቶ በማሳየት አካታች እና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክር እንዲጀመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ባለድርሻ አካላት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል።

የመንግስት እና የግል ሚዲያዎች ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ዜጎች በቂ መረጃ እና እውቀት እንዲያገኙ ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራ ሰርተዋል። ልዩ ልዩ የመንግስት አካላት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መቃናት ልዩ ልዩ ድጋፍ አድርገዋል።

ከሁሉም በላይ የምክክሩ ዋና አስተባባሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቱ በተቻለ መጠን በስኬት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሀገራዊ ምክክሩ ከሀሳብ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር፣ ከዝግጅት ምእራፍ እስከ ምክክር ጉባኤው መጠናቀቅ አስተዋጾ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በምክክሩ ስምምነት የተደረሰባቸው ምክረ ሀሳቦች በቀጣይ ወደ መሬት ወርደው በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረጉ ከሚመለከታቸው አካላት በተለይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እያረጋገጠ፣ እስከ አሁን በሂደቱ የተሳተፉ አካላት የሀገራዊ ምክክሩ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እስኪሆኑ ድረስ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ያቀርባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review