የከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት ላይ የምክር ቤቱ ሚና የላቀ ነው- አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር

AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባለፉት አምስት አመታት የከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት ላይ ሚናው የላቀ መሆኑን የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር ተናገሩ።

ምክር ቤቱ በ3ኛው ዙር የሥራ ዘመኑ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር በላቀ አፈጻጸም እንዲያከናውን አስተዋጽኦ ለነበራቸው ተጠሪ ተቋማት፣ የክፍለ ከተማ ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች እና ቋሚ ኮሚቴዎች እውቅና ሰጥቷል።

በእውቅና መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር፤ ከተማዋ ባለፉት አምስት አመታት ለከተማዋ ነዋሪዎች ፋይዳ ያላቸውና ቀጣይነት ያለው ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል።

ምክር ቤቱም በዚህ እድገት ውስጥ ሚናው ከፍ ያለ ነበር ያሉት አፈጉባኤዋ፤ የነዋሪው ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለው ተሳትፎም እንዲያድግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

አስፈጻሚ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ፣ የከተማዋ ውስን ሀብት የሆነው በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል እንዲሁም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን መወጣቱንም ገልጸዋል።

በእነዚህ ተግባራትም የከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ መደረጉን ነው አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር የገለጹት።

ምክር ቤቱ የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ ለዚሁ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እውቅና ሰጥቷል።

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review