የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገር አዲስ ምዕራፍን የከፈተ እና ለኢትዮጵያዊያን የተበሰረ ድል ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገር አዲስ ምዕራፍን የከፈተ እና ለኢትዮጵያዊያን የተበሰረ ድል ነው

AMN – ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገር አዲስ ምዕራፍን የከፈተ እና ለኢትዮጵያዊያን የተበሰረ ድል መሆኑን በሀገራዊ ምክክሩ የተሳተፉ ጋዜጠኞች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከጅማሮው እስከ ፍጻሜው ድረስ ለታዳሚዎች መረጃዎችን በማድረስ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና ተወጥተዋል።

ሀሰተኛ መረጃ ሀገርን ከፍ ሲልም ዓለምን ማወክ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ በሚዛናዊነት እና በምክንያታዊነት የሙያ ስነ ምግባርን ባከበረ አካሄድ ሀሰትን በእውነት ድል በመንሳት ረገድም የማይነጥፍ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

ከዚህ ባለፈም ከዘገባ አኳያ በሀገራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ ለሀገር ሀሳብን በማዋጣት በኩል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሚና የሚዘነጋ አይደለም።

በምክክሩ ላይ የተሳተፈው የኤ ኤም ኤን ጋዜጠኛ ምትኩ ተሾመ፤ ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊነቱ በግልጽ የተገለጠበት መሆኑን ተናግሯል።

ምክክሩ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ጥላ ስር አሰባስቦ ስለ ሀገር በመምከር፣ ለሀገር ጠቃሚ ሃሳቦችን እንዲያዋጡ ያስቻለ መሆኑንም ገልጿል።

በሀገራዊ ምክክር ቃለ ጉባኤ በመያዝ ላይ የተሳተፈው ጋዜጠኛ ምሩጽ ተስፋይ በበኩሉ፣ ምክክሩ ግልጽነትን የተላበሰ እንደነበር ተናግሯል።

ምክክሩ በመከባበር ላይ የተመሰረተ እና ለሀገር አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት መሆኑን ደግሞ በምክክር ጉባኤው ላይ የተሳተፈው ሌላኛው ጋዜጠኛ ተክለሀይማት ገብረአየዝጊ ገልጿል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የሀገራዊ ምክክሩን ከጅማሮው እስከ ፍጻሜው ድረስ መረጃዎችን በማድረስ የነበራቸወ ሚና በታሪክ መዝገብ ላይ የተከተበ መሆኑን ተሳታፊ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙኃኑ የምክክር ሂደቱን በማሳየት ከጉባኤው ጅማሮ እስከ ፍጻሜው በትጋት ሚናቸውን የተወጡበት መሆኑን ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ታሸንፍ ዘንድ አሰባሳቢ ሃሳቦች የተነሱበት እና ለሀገርም አዲስ ምዕራፍን የከፈተ መሆኑን የገለጹት ጋዜጠኞቹ፣ ለተግባራዊነቱ መስራት የመገናኛ ብዙሃኑ ኃላፊነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

በተመስገን ይመር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review