AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ማሳደጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በ2018 አፈፃፀም እና በ2019 አፈፃፀሙ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በ2018 የኢትዮጵያ ሀይል የማመንጨት አቅም 9 ነጥብ 730 ሜጋ ዋት ደርሷል ብለዋል፡፡

ይህ አሀዝ ከ2017 የበጀት አመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ23 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ከውጭ ምንዛሬ አንፃር በ2018 የበጀት አመት 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላርን ከሀይል ሽያጭ ማግኘት መቻሉንም ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል፡፡
ሀይልን የማመንጨት እና ከዉጭ ምንዛሬ የማግኘት አቅም ባለፉት አመታት ከተጠናቀቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተገኘ ስኬት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሚናም ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም የሀይል አማራጮችን በማስፋት አስተማማኝ ሀይል የማመንጨት አቅምን ለመገንባት እንደሚሰራ በጋዜጣዊ መግለጫዉ ላይ ተነስቷል፡፡
በተመስገን ይመር