AMN-ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ የቻይናው መሪ ዴንግ ዚያኦፒንግ ሼንዜን (Shenzhen) ከተማን የመጀመሪያዋ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን (SEZ) አድርገው ሲመርጡ፣ አላማቸው አንድ ነበር— ትንሽ የዓሳ አጥማጆች መንደር የነበረችውን አካባቢ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ሞተር ማድረግ።
ዛሬ ላይ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጅምሩ በተመሳሳይ የልህቀት፣ የኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን እይታ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ተምሳሌት ለመሆን እየገሰገሰ ይገኛል።
የሼንዜን ስኬት ምስጢር የነበሩት ዋና ዋና መርሆች በገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እየሆኑ እንደሚገኙ በዝርዝር መመልከት ይቻላል።
* የኢኮኖሚ እና የፖሊሲ ሙከራ ቦታ (Economic Lab)፦ ሼንዜን ሙሉ በሙሉ ሶሻሊስት የነበረችውን ቻይና ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር እንደ መሞከሪያ እንደነበረች ሁሉ፣ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ምርቶችን፣ የወጪ ንግድን እና ገቢ ምርትን የመተካት (Import Substitution) ስትራቴጂዎችን በተግባር የሚያስመሰክር፣ ለሀገሪቱ አዲስ የኢንዱስትሪ ልህቀት ሞዴል ሆኖ የሚያገለግል የሙከራ ማዕከል ነው።
* የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማሳቢያ ማዕከል፦ ሼንዜን የውጭ ኩባንያዎችን (FDI) ለመሳብ የቀረጥ ነፃ መብቶች፣ ዝቅተኛ ታክስ እና የተቀላጠፈ የአንድ ማዕከል አገልግሎት (One-Stop Shop) ዘርግታ እንደነበር ይታወቃል።
ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክም አልሚዎችና አምራቾች ያለ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ በምቾት እንዲሰሩ የተቀላጠፈ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማዘጋጀት፣ ፈቃድ፣ ታክስ እና ሌሎች አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ባንድ ማዕከል በማቅረብ ኢንቨስትመንትን በስፋት ይስባል።
* የቴክኖሎጂ፣ የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር፦ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ የአመራር ጥበብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የሼንዜን ከተማ የሀገር ውስጥ አቅምን እንደገነባች ሁሉ፣ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክም ዘመናዊ የፋብሪካ አመራር፣ የጥራት ቁጥጥር እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በመተግበር የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም ይገነባል፤ ምርታማነትንም ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋግራል።
* የተቀናጀ መሰረተ ልማት እና የሥራ እድል ፈጠራ፦ በሼንዜን ከተካሄደው ፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተመሳሳይ፣ ገላን ጉራ የተሟሉ የፋብሪካ ሼዶች፣ መንገድ፣ የኃይል እና የመገናኛ አወቃቀሮችን በማቅረብ ለአካባቢውና ለሀገሪቱ ዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር የአካባቢውን ኢኮኖሚ ህይወት ይለውጣል።
በጥቅሉ ሼንዜን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከትንሽ መንደር ተነስታ የዓለም የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል (“Silicon Valley of Hardware”) መሆን የቻለችው በጽኑ ራዕይ እና በስትራቴጂካዊ አመራር ነው።
ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክም በአገሪቱ የማኑፉክቸሪግ ዘርፍ የታለመዉን የትራንስፎርሜሽን መንገድ በመከተል፣ የምርት አቅምን በማሳደግ፣ የወጪ ንግድን በማስፋፋት እና የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ህዳሴ መሪ ምልክት የመሆን ራዕዩን ከወዲሁ እውን እያደረገ ይገኛል።
በዘመን ጁነዲን
(የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ማርኬቲንግ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ)