AMN- ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም
ህዝባችንንና የልማት አጋሮቻችንን በማስተባበርና ተሞክሮዎችን በማስፋት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሀገራዊ ማንሰራራት ውስጥ የአዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ እንተጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ዛሬ የከተማ አስተዳደራችንን የቀጣይ አምስት ዓመታት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት መላው የከተማችን አመራሮች በተገኙበት አስጀምረናል ብለዋል፡፡
በስድስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ህዝባችን የሰጠንን ሃላፊነት መነሻ ያደረገ ስትራቴጂክ እቅድ ነድፈን ቃላችንን በተግባር ቆጥረን ፈፅመን የከተማችን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም ከተማችን ደግሞ ተወዳዳሪ እንድትሆን አድርገናልም ነው ያሉት፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግ የከተማችን ነዋሪ እምነት አድሮበት ዳግም መርጦን ኃላፊነት ሰጥቶናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ውይይቱም የከተማችን ነዋሪ የጣለብንን እምነት እና የሰጠንን ሀላፊነት መነሻ ያደረገ፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት እና የ2019 በጀት ዓመት የእቅድ ዝርዝር ግቦች ላይ ተወያይተን በማዳበር የባለፉት አምስት ዓመታት አፈፃፀምን በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጁነታችንን የምናረጋግጥበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን ዝርዝር ውይይቶች ስናደርግ 24/7 የመፈጸም ባህላችንን ይበልጥ በማሳደግ፣ አመራራችን ከፊት ሆኖ የበለጠ እየሮጠ ህዝባችንንና የልማት አጋሮቻችንን በማስተባበርና ተሞክሮዎችን በማስፋት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሀገራዊ ማንሰራራት ውስጥ የአዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ እንተጋለን ሲሉም ገልጸዋል።
ከንቲባዋ አክለውም፤ በተጨማሪም በክረምት የያዝናቸው የ90 ቀን ስራዎች ውስጥ የ60 ቀናት አፈፃፀማችንንም የምንገመግምበት የውይይት መድረክ ነው ብለዋል።